ትራምፕ በካናዳ ፣ ሜክሲኮ እና ቻይና ላይ የታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ተከትሎ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሀገራት እነማን ናቸው?
ብሪታንያን እና የእስያ ሀገራት የታሪፍ ጭማሪ የተደረገባቸው ሀገራት አማራጭ የገበያ መዳረሻ ይሆናሉ ተብሏል

የታሪፍ ጭማሪው በአንድ አሜሪካዊ ቤተሰብ ላይ እስከ 300 ዶላር ታክስ እንደመጨመር ነው ተብሏል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጎረቤቶቻቻው ሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ የ25 በመቶ እንዲሁም በኢኮኖሚ ተገዳዳሪያቸው ቻይና ላይ የ20 በመቶ ታሪፍ ተግባራዊ አድርገዋል፡፡
ቤጂንግ ወደ ዋሽንግተን የምትልካቸው የሞባይል ስልኮች ፣ የኮምፒውተር መለዋወጫዎች የኤሌክትሪክ እና የኢንዱስትሪያል ግብአቶች ፣ የህጻናት መጫዎቻዎች (አሻንጉሊቶች) ፣ የቤት እቃዎች ፣ የአሳ ምርቶች ፣ አኩሪ አተር ፣ ስጋ እና እና ጥጥ የመሳሰሉ ምርቶች እስከ 20 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል፡፡
ቻይና በሰጠችው የአጸፋ ምላሽ በአሜሪካ የግብርና ምርቶች ላይ የ15 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ገቢራዊ ያደረገች ሲሆን ከዚህ ባለፈም የአሜሪካ ኩባንያዎች የሚሳተፉባቸውን ዘርፎች ክልከላ በእጥፍ አሳድጋለች፡፡
በተመሳሳይ ካናዳ በኢነርጂ እና በሌሎች የአሜሪካ ምርች ላይ ውሳኔዎችን ስታሳልፍ ሜክሲኮ በበኩሏ የታሪፉን ተጽዕኖ ለመቋቋም አማራጭ መንገዶች ማዘጋጀቷን ይፋ አድርጋለች፡፡
ቢቢሲ በዘገባው እነዚህ ተጨማሪ ታክሶች አሜሪካውያን ከ1930ዎቹ ጀምሮ ወደ ሀገራቸው በሚገቡ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛውን የታሪፍ ጭማሪ እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል ብሏል፡፡
ታሪፍ የተጨመረባቸው ሸቀጦች የሚያከፋፍሉ አሜሪካውያን ነጋዴዎች አነስተኛ የትርፍ ህዳግ ስለሚኖርባቸው የታሪፉን ወጪ ለመሸፈን በፍጥነት የዋጋ ጭማሪ ገቢራዊ ሊያደርጉ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት በአሁኑ ወቅት ከተጠበቀው በላይ ማሻቀቡን ገልጸው በዚህ አመት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የበለጠ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከምግብ እስከ ኢንዱስትሪ ግብዐቶች በአሜሪካ ገበያ ሰፊ ድርሻ ባላቸው ሀገራት ላይ የተጣለው ታሪፍ በአንድ አሜሪካዊ ቤተሰብ ላይ 300 ዶላር ታክስ እንደመጨመር ነው ተብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትራምፕ የንግድ ጦርነት ኢላማ ውጪ የሆኑ ሀገራት በዚህ አጋጣሚ ከፍተኛ ጥቅም ሊያጋብሱ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡
ለአብነት ቬትናም እና ማሊዢያ በታሪፉ ምክንያት ቻይና ወደ አሜሪካ የምትልካቸውን ምርቶች መቀነስ ተከትሎ ይህን ክፍተት ለመሙላት ከፊት መሰለፋቸው እየተነገረ ነው፡፡
እነዚህ ሀገራት የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን አለፍ ሲልም የግብርና ሸቀጦችን ወደ አሜሪካ በመላክ ከታሪፍ ጭማሪ የጸዳ ትርፍን ሊሰበስቡ ይችላሉ፡፡
ሌላኛዋ ተጠቃሚ ሀገር ብሪትንያ ስትሆን ብሪታንያ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ የታሪፍ ወጥመድ የምታመልጥ ከሆነ በአጋጣሚው ሰፊ የንግድ ግንኙነት እና ከከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡
ለንደን በአሜሪካ የተገፉ ሀገራት አማራጭ የገበያ መዳረሻ በመሆን ሸቀጦችን በአነስተኛ ዋጋ የማግኘት እድልም ይኖራታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በታሪፍ ጭማሪው ንግዳቸው አደጋ ውስጥ የሚገባባቸው አምራች እና አከፋፋዮች መዳረሻቸውን ወደ ብሪታንያ በመቀየር ምርታቸውን ከታሪፍ ነጻ ወደ ዋሽንግተን ሊያሳልፉ እንደሚችሉ ነው የተዘገበው፡፡