
የዲፕሲክ ኤአይ ሞዴል መስራች በቅርቡ በፓሪስ በተካሄደው የኤአይ ጉባኤ ላይ እንዲገኝ ቢጋበዝም በፍራቻ ምክንት ሳይገኝ ቀርቷል ተብሏል
ቻይና የኤአይ ባለሙያዎቿ ወደ አሜሪካ እንዳይጓዙ አገደች፡፡
የዓለም ቴክኖሎጂ የበላይ ለመሆን ብርቱ ፉክክር ላይ የሚገኙት አሜሪካ እና ቻይና አሁን ደግሞ ፉክክራቸው ወደ ኤአይ ዞሯል፡፡
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር በዋናነት የቻይናን የበላይነት የመግታት ግልጽ እቅድ አለው የተባለ ሲሆን የቻይና ባለሙያዎች የአሜሪካንን ቴክኖሎጂዎች ይሰርቃሉ ብለውም ያምናሉ፡፡
ለአብነትም ከአንድ ወር በፊ ይፋ የሆነው ዲፕሲክ ኤአይ ሞዴል በርካታ የአሜሪካ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን አስደንግጧል፡፡
ይህን ተከትሎም አሜሪካ የኤአይ ባለሙያዎችን ልታስር እና መረጃዎችን አሳልፈው እንዲሰጡ ልትደራደር ትችላለች በሚል የጉዞ እቀባ ማድረጓን ዎልስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ የቻይና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች ራሳቸውን ከጉዞ እንዲያርቁ ታዘዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የዲፕሲክ ኤአይ ሞዴል መስራች እና ስራ አስኪያ ሊያንግ ወፌንግ ባሳለፍነው ሳምንት በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኤአይ ጉባኤ ላይ እንዲገኝ የቀረበለትን ግብዣ ሳይቀበል ቀርቷል ተብሏል፡፡
ባለሙያዎቹ የግድ መሄድ ካለባቸውም አስቀድመው ለቻይና መንግስት ስለ ጉዟቸው እቅድ፣ ማንን ሊያገኙ እንደሚችሉ እና የጉዟቸው ቆይታ መረጃ እንዲሰጡ ታዘዋል፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ በሀገሪቱ አሉ የተባሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እና መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በመንግስታቸው እንዲተማመኑ እና ተሰጥኦዎቻቸውን ሁሉ ለዓለም እንዲያሳዩ ማሳሰባቸው ተገልጿል፡፡