ቻይና የኤሌክትሪክ መኪናን በ10 ደቂቃ መሙላት የሚያስችል ቻርጀር መስራቷን ገለጸች
አሁን ላይ ተመራጭ የሚባሉት በአሜሪካው ቴስላ እና በቻይናው ቢዋጂ ኩባንያዎች የተሰሩት ናቸው
የዓለማችን ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ መኪኖችን በአጭር ጊዜ የሚሞላ ቻርጀር ለመስራት በፉክክር ውስጥ ናቸው
ቻይና የኤሌክትሪክ መኪናን በ10 ደቂቃ መሙላት የሚያስችል ቻርጀር መስራቷን ገለጸች፡፡
በዓለማችን ለይ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ፍላጎት እና ምርት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ይሁንና እነዚህን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንደ ልባቸው ሊስተናገዱበት የሚችሉት ቻርጀር ማግኘት አደጋች ሆኗል፡፡
ሌላኛው አስቸጋሪ ነገር ደግሞ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ለማድረግ የሚፈጀው ጊዜ ረጅም መሆን ሲሆን በየጊዜው እየተሻሻለ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡
የቻይናው ዚከር የቴክኖሎጂ ኩባንያ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በቶሎ ቻርጅ ለማድረግ መላ አግኝቻለሁ ብሏል፡፡
ኩባንያው እንዳስታወቀው አንድን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪን በ10 ደቂቃ ውስጥ 80 በመቶ መሙላት የሚያስችል ቴክኖሎጂ መስራቱን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካው ቴስላ ኩባንያ አንድን ተሽከርካሪ በ15 ደቂቃ ባትሪ መሙላት የሚያስችል ቻርጀር በማምረት በገበያ ላይ አስተዋውቋል፡፡
የዓለማችን የቴክኖሎጂ ኩባያዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ የሚሞላበትን ጊዜ ለማሳጠር በሙከራዎች ላይ ሲሆኑ የዓለም ገበያን እየተቆጣጠሩ የመጡት የቻይና ኩባንያዎች አዲስ ፈጠራ ይፋ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የቻይና ኩባንያዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን በማምረት እና ተያያዥ የሆኑ አዳዲስ ፈጠራዎችን ለዓለም ገበያዎች በማቅረብ ዋነኛ ተወዳዳሪ የሆኑ ሲሆን አሜሪካን እና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የቻይናን ግስጋሴ ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡
ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ የእንግሊዙ ኒዮቦልት የቴክኖሎጂ ኩባንያ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በቶሎ ቻርጅ ለማድረግ መላ አግኝቻለሁ ማለቱ አይዘነጋም፡፡
ኩባንያው እንግዶች በተገኙበት በአራት ደቂቃ ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪን እንደሚሞላ አረጋግጧል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሙከራ ደረጃ ያለው ይህ ቴክኖሎጂ በ2025 በገበያ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል፡፡