ወደ ታዋቂው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በተከታታይ 16 ዓመታት ብሄራዊ ፈተና የወሰደው ቻይናዊ
የ36 ዓመቱ ቻይናዊ ታዋቂው ሲንጉዋ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ነው ተከታታይ ሙከራ እያደረገ ያለው
“ግትር ሰው” የተባለው ግለሰቡ ለሌላ ዩኒቨርሲቲ የሚበቃ ውጤት ቢያመጣም “ከሲንጉዋ ውጪ አልፈልግም” ብሏል
የ36 ዓመቱ ቻይናዊ ህልሙ ወደ ሆነው ታዋቂው እና ለመግባት ከባድ ወደ ሆነው ዪኒቨርሲቲ ገብቶ ለመማር እያደረገ ባላው ጥረት የቻይና በጣም ግትሩ ሰው የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።
ታንግ ሻንግጁን የተባለው የ36 ዓመቱ ቻይናዊ ወደ ታዋቂው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በተከታታይ 16 ዓመታት ብሄራዊ ፈተና መውሰዱም ተነግሯል።
ታንግ በጣም ከባድ እንደሆነ የሚነገርለትን የቻይና ብሄራዊ የኮሌጅ መግቢያ ፈተናን ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈተነው በፈረንጆቹ 2009 ላይ ሲሆን፤ በወቅቱም ከ750 ማምጣት የቻለው 372 ነጥብ ሲሆን፤ ይህም ህልሙ ወደ ሆነው ሲንጉዋ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በቂ አልነበረም።
ተስፋ ያልቆረጠው ታንግ ሻንግጁን ለተከታታይ ዓመታት ሳይታክት በርትቶ በማጥናት ብሄራዊ ፈተናውን መፈተኑን የቀጠለ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2016 ላይ ከፍተኛ የሆነውን 625 ነጥብ ማምጣት ችሎም ነበር።
ታንግ በ2016 ያመጣው 625 ነጠብ ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስገባው ቢሆንም አሁንም ህልሙ ወደሆነው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ግን በቂ አልነበረም።
ከዓመት ዓመት ጥረቱን የቀጠለው ታንግ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚቀርቡለትን እደል ወደ ጎን በመተው ሲንጉዋ ዩኒቨርሲቲ የመግባት ህልሙን ሲከተል ቆይቷል።
በ2019 ላይም በብሄራዊ ፈተናው ከ750 ነጥብ 649 ማምጣት ወደ ህልሙ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባወን ነጥብ ቢያገኘም በፊዚክስ እና በኬሚስትሪ የትምህርት አይነት ለመከታተል በቂ ስላልሆኑ ትግሉን መቀጠሉንመ ይናገራል።
ታንግ ብሄራዊ ፈተናውን መፈተኑን ቢቀጥልም እንዳለመታደል ሆኖ ከ649 ውጤቱ በላይ ግን ማምጣት እንዳልቻለ ነው የተነገረው።
በመጨረሻም ታንግ እጅ በመስጠት ባሳለፍነው ዓመት ላይ ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲ ተመግባ ፊዚክስና ኬሚስትሪ ለማጥናት ወስኖ ብሄረዊ ፈተና ቢፈተንም፤ ከ750 ውጤት 594 በማምጣት ሳይሳካለት ቀርቷል። ምክንያቱ ደግሞ እሱ መማር የሚፈልገው ትምህርት 608 እና ከዚያ በላይ ያመጡ ተማሪዎችን ስለተቀበለ ነው።
ዘንድሮ ለ16ኛ ጊዜ የብሄራዊ ፈተናን የተፈተነው ታንግ ከ750 ውጤት 600 ውጤት ያመጣ ሲሆን፤ ውጤቱ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባው ቢሆን አሁንም ህልሙ የሆነውን ፊዚክስና ኬሚስትሪ ለማጥናት የሚያበቃውን ውጤት ሳያገኝ ቀርቷል።
“የቻይና ግትሩ ሰው” የሚል ቅጽል መጠሪያ የተሰጠው ታንግ፤ አሁን ላይ ግን ተሳክቶለት የሚፈልገውን ትምህርት ቢያጠና እንኳ ስራ የማግኘት እድሉ ከባድ እንደሚሆንበት እየተረዳ የመጣ ሲሆን፤ ምክንያ ደግሞ ተመርቆ ሲወጣ ለስራ ቅጥል የሚወዳደረው እድሜያቸው በ20ዎቹ ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር በመሆኑ ነው።
ባለፉት 16 ዓመታት የተለያዩ ስራዎችን በመስራት እራሱን እና አያቶቹን ሲደግፍ የነበረው ታንግ፤ አሁን ላይ ግን ብሄራዊ ፈተና ላይ የሚያደርገውን ትኩረት በመተው ሙሉ በሙሉ በስራ ላይ ማተኮር እንደሚፈልግም ተናግሯል።
በቀጣይ ዓመት የኮሌጅ መግቢያ ብሄራዊ ፈተናን ስለመውሰዱ ግን አሁንም በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም ነው የተባለው።