በ2020 ከተፈጠረና ቢያንስ 20 የህንድ ወታደሮች ከተገደሉ ወዲህ የተፈጠረ የመጀመሪያው ግጭት ነው
የሕንድ እና ቻይና በሚወዛገቡበት ድንር ላይ የሁለቱ ሀገራት ወታደሮች መካከል ግጭት መፈጠሩ ተገለፀ።
ከረንጆቹ ሰኔ 2020 በሁለቱ ወታደሮች መካከል በተፈጠረና ቢያንስ 20 የህንድ ወታደሮች ከተገደሉ ወዲህ የተፈጠረ የመጀመሪያው ግጭት ነው ተብሏል።
ከቀናት በፊት በህንድ አሩናቻል ፕራዴሽ ግዛት በታዋንግ አከባቢ በተፈጠረ ግጭት የህንድ እና የቻይና ወታደሮች ቀላል የተባለ ጉዳት አጋጥሟቸዋል።
የህንድ ጦር እንዳለው በሁለቱ ጎረቤቶች መካከል በፈረንጆቹ ሰኔ 2020 ከተከሰተው “ገዳይ” ግጭት በኋላ ይህ የመጀመሪያ ነው ብሏል።
ከግጭቱ በኋላ “ሁለቱም ወገኖች ወዲያውኑ ከአካባቢው ርቀዋል” ያለው የህንድ ጦር፤ ድርጊቱን ተከትሎ በአካባቢው የሚገኘው አዛዥ ከቻይና አቻቸው ጋር በጉዳዩ ላይ መምከራቸውን ተናግሯል።
የሕንድ መከላከያ ሚንስትር ራጅናት ሲንግ ለፓርላማ እንደተናገሩት የሕንድ ወታደሮች የቤጂንግ ወታደሮች በፈረንጆቹ ታህሳስ ዘጠኝ ወደ ህንድ ግዛት እንዳይገቡ በመከልከላቸው በሁለቱም ወገኖች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት የሆነውን ግጭት ተከስቷል።
በታህሳስ 9 በቻይና እና በህንድ ወታደሮች መካከል የእጅ ለእጅ ጦርነት ተካሄዷል ነው የተባለው።
“የህንድ ወታደሮች የቻይና ህዝባዊ ጦር ወታደሮች ወደ ግዛታችን እንዳይገቡ አስቆመዋል” ሲሉም ሚኒስቴሩ ተናግረዋል።
ቻይና በበኩሏ ከህንድ ጋር በምትጋራው ድንበር ላይ ሁኔታው የተረጋጋ ነው ማለቷን ቲ.አር.ቲ ዘግቧል።
"እስከምንረዳው ድረስ የቻይና-ህንድ የድንበር ሁኔታ በአጠቃላይ የተረጋጋ ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ተናግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች "በድንበር ጉዳይ ላይ በዲፕሎማሲያዊ እና በወታደራዊ ንግግሮች ያልተደናቀፈ ውይይት አድርገዋል" ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።
አሩናቻል ፕራዴሽ በህንድ ምስራቃዊ ጫፍ ላይ የምትገኝ ግዛት ስትሆን፤ ሀገሪቱ ከቻይና ጋር ድንበር የምትጋራባትም ናት።
የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርና የመከላከያ ሚንስቴር በግጭቱ ወቅት የሕንድ ወይም የቻይና ወታደሮች የደረሰባቸውን ጉዳት በተመለከተ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም ሆነ በኒው ዴሊ የሚገኘው ኤምባሲው አስተያየት ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡም ተብሏል።
ያልተከለለው የሀገራቱ 3 ሺህ 800 ኪ.ሜ የእስያ ግዙፍ ድንበር እ.ኤ.አ. በ1962 ከተካሄደው ጦርነት ወዲህ ሰላማዊ ሆኖ ቆይቷል።
ከሁለት ዓመት በፊት የተፈጠረው ግጭት የሀገራቱን ግንኙነቱ በአፋጣኝ ወደ ውጥረት ቀይሮታል ተብሏል።