የሁለቱ ኮሪያዎች ድንበር በመድፍ ጩኸት መታወኩን ቀጥሏል
ትናንት ከ130 በላይ መድፎችን ወደ ደቡብ ኮሪያ የተኮሰችው ፒዮንግያንግ ዛሬም ተጨማሪ መድፍ ሲተኮስ እንዲውል ትዕዛዝ ሰጥታለች
ሰኞ እለት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የጀመሩት ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካም የአጻፋ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ እያስጠነቀቁ ነው
ሰሜን ኮሪያ ለሁለተኛ ተከታታይ ቀን ወደ ጎረቤቷ መድፍ እንዲተኮስ አዘዘች።
በቸርወን ግዛት የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እያደረጉ የሚገኙት ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ወደ ድንበሬ አቅራቢያ ሮኬት ተኩሰዋል በሚል ነው ፒዮንግያንግ ትዕዛዙን ያስተላለፈችው።
ዋሽንግተን እና ሴኡል የጋራ ወታደራዊ ልምምዳቸውን ካላቆሙ የመድፍና ሚሳኤል ተኩሱ እንደሚቀጥል መዛቷንም ነው ኬ ሲ ኤን ኤ የተሰኘው የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ያስነበበው።
ፒዮንግያንግ ትናንት 130 መድፎችን ከደቡብ ኮሪያ ጋር በምትዋሰንበት በምዕራብ እና በምስራቃዊ የባህር ዳርቻ መተኮሷ ይታወሳል። የተወሰኑትም ሀገራቱ ከጦር ነጻ ቀጠና እንዲሆን በተስማሙበት የድንበር አካባቢ ማረፋቸው ተገልጿል።
የሴኡል ባለስልጣናት ይህን የፒዮንግያንግ እርምጃ ሀገራቱ በ2018 የተፈራረሙትን ስምምነት አደጋ ላይ ጥሏል በሚል ተቃውመውታል።
የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አዛዦችም ትናንት በሰጡት መግለጫ ከሰሜን ኮሪያ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውም ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
ፒዮንግያንግ በዚህ የፈረንጆቹ አመት ብቻ 63 የባለስቲክ ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች። ይህም ካለፈው አመት ከሁለት እጥፍ በላይ መሆኑን ነው የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ የዘገበው።
አሜሪካ በበኩሏ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና ሌሎች የቀጠናው ሃገራትን በማስተባበር ትንሿን ሀገር አደብ ለማስገዛት ጥረት ማድረጓን ቀጥላለች።
ከሀገራቱ ጋር የምታደርገውን የምድር፣ የባህር እና አየር ሃይል ልምምድም ገፍታበታለች።
ይህ ወታደራዊ ልምምድን እንደ ብሄራዊ ደህንነት ስጋት የምትመለከተው ፒዮንግያንግ ቁጣዋን እንደተለመደው በመድፍ ተኩስና በሚሳኤል ማስወንጨፍ እየገለጸች ነው።