ኢራቅ ከኢራንና ተርኪዬ በሚያዋስናት ድንበር የፌዴራል ጦሯን “በድጋሚ ላሰማራ ነው” አለች
ባግዳድ ጦሬን አሰማራለሁ ያለችው በኩርዲስታን ክልል ሁለቱ ጎረቤቶቿ ተደጋጋሚ የቦምብ ድብደባ ማድረሳቸውን ተከትሎ ነው
በኢራን ተቃውሞና በተርኪዬ ሰሞነኛ ጥቃት ምክንያት ቀጣናው ውጥረት ገጥሞታል
ባግዳድ ከኢራን እና ተርኪዬ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ የፌዴራል ጠባቂዎችን እንደገና ለማሰማራት ማቀዷን ገልጿለች።
ሀገሪቱ ይህን የወጠነችው በኢራቅ ራስ ገዝ ኩርዲስታን ክልል ተቃዋሚዎች ላይ ከሁለቱም ጎረቤቶቿ ተደጋጋሚ የቦምብ ድብደባ ከደረሰ በኋላ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሺአ አል-ሱዳኒ ይመራል የተባለ የመንግስት የጸጥታ ስብስብ ባወጣው መግለጫ “የኢራቅ ድንበር ጠባቂዎች በኢራን እና ተረኪዬ ድንበር ለማሰማራት ተወስኗል” ብሏል።
ይህ ተነሳሽነት ከኩርዲስታን ክልል መንግስት እና ከኩድር ወታደራዊ ኃይል ጋር በመተባበር መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ የኩርድ ክልላዊ ኃይል አለቃ በስብሰባው መሳተፋቸው ታውቋል።
የኢራቅ ኩርዲስታን ድንበሮች በአሁኑ ጊዜ በባግዳድ ፌደራል መከላከያ ሚንስቴር ስር ባለው ፔሽመርጋ በተባለው ኃይል እንደሚጠበቁ ድፌንስ ፖስት ዘግቧል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴን አሚር-አብዶላሂን የቴህራን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በኢራቅ ኩርዲስታን ውስጥ የባግዳድ ኃይሎች በድንበር ላይ እስኪሰፍሩ ድረስ ይቀጥላል ብለዋል። "ከእንግዲህ የግዛታችንን አንድነታችንን ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ አያስፈልገንም" ሲሉ ስለ ኢራቅ ውሳኔ ተናግረዋል።
የኩርዲስታን ክልላዊ መንግስት የፔሽሜርጋን ጦር በድንበር ላይ ማጠናከሪያ አድርጎ እንደሚልክ ከወዲሁ ተነግሯል።
የኢራቅ ኩርዲስታን እ.አ.አ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በርካታ የኢራን-ኩርዲሽ ተቃዋሚ ቡድኖችን በማገዝ ይታቃል። እነዚህ ቡድኖች ቀደም ባሉት ጊዜያት በቴህራን ላይ የታጠቁ ዓመፅ ያነሱ ናቸውም ተብሏል።
ታጣቂዎቹ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንቅስቃሴያቸው እየቀነሰ ቢመጣም በኢራን የተቀሰቀሰው የተቃውሞ ማዕበል እንደገና ውጥረቱን ቀስቅሷል ነው የተባለው።
ከሳምንታት በዲት በተርኪዬ ኢስታንቡል የኩርዲስታን የሰራተኞች ፓርቲ አደረሰው የተባለን ጥቃት ተከትሎ አንካራ በኢራቅ እና ሶሪያ ክፍሎች ያሉ የኩርድ ኃይሎችን ያነጣጠረ የአየር ጥቃት ዘመቻ ጀምራለች።