“የራስን እሴቶች ሌሎች እንዲቀበሉ ማስገደድ ሌሎችን የመጫን ድርጊት ነው” የዩኤኢ ውጭ ጉ/ሚኒስትር
“የምዕራባውያን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አይወክልም” ስትል ቻይና ገልጻለች
ቻይና እና ዩኤኢ በሽብርተኝነት ፣ ፅንፈኝነትና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
ቻይና እና ዩኤኢ “ሽብርተኝነትና ፅንፈኝነትን” በጋራ ለመከላከል የሚያደርጉትን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተስማሙ፡፡
የቻይና የምክር ቤት አባልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ዪ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በአቡ ዳቢ መክረዋል፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ፣ ቻይና እና ዩኤኢ ሽብርተኝነትና ፅንፈኝነትን ለመከላከል የሚያደርጉትን ትብብር ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡
“የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የቆየ ወንድማማችነትና አጋርነት አላቸው” ያሉት ዋንግ ዪ፣ የቻይና-ዩኤኢ ግንኝነት በከፍተኛ መተማመን ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የሁለቱም ሀገራት መሪዎች የጠበቀ ወዳጅነት ፣ ለሀገራቱ ቀጣይነት ያለውና ጠንካራ ግንኙነት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ነው የገለጹት፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ የሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ልማት የዓለም ሰላማዊ ኃይሎች እድገት እና የስልጣኔዎች ብዝሃነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው ፣ ይህም “ዓለምን ይበልጥ ሚዛናዊ ፣ ተስማሚ እና ውብ የሚያደርግ ነው” ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ “ቻይና ከዩኤኢ ጋር ያለትን የትብብር ማእቀፍ በማስፋት እና ቀጣይነት ያለው ትብብር እውን በማድረግ ዓለም አቀፍ የሞራል ኃላፊነቷን ትወጣለች” ብለዋል፡፡
የሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ “በተለይ የምዕራባውያን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አይወክልም” ያሉት ዋንግ ስለሆነም “በሌሎች ሀገሮች አስተያየት ሳይሆን የአንድ ሀገር የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በሕዝቦቿ መዳኘት አለበት” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“በተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች የሚገኙ የተለያዩ ስልጣኔዎች እና ባህሎች ከሰብዓዊ መብት አንጻር የተለያዩ ግንዛቤዎች እና ትኩረቶች እንዲኖሩ ማድረጋቸው የተለመደ ነገር ነው” ያሉት ዋንግ “በእኩልነት መግባባት እና በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ እርስ በእርስ መማማርን የምንደግፈው ለዚህ ነው” ብለዋል፡፡
የዩኤኢ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ በበኩላቸው ፣ ሀገራቸው ከቻይና ጋር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በተለይም የፀረ-አክራሪነት እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር እና በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስጠበቅ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
“የራስን እሴቶች ሌሎች እንዲቀበሉ ማስገደድ ሌሎችን የመጫን ድርጊት ነው” ያሉት ሼኩ ፣ በርካታ “ታዳጊ ሀገራት በሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ እንደዚህ ያለ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት ተፈጽሞባቸዋል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሰብዓዊ መብቶችን በማስጠበቅ ረገድም ዩኤኢ ከቻይና ጋር ለመስራት ፈቃደኛ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነትን ለማረጋገጥም በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በስድስት ሀገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት በአውሮፓውያኑ መጋቢት 24 የጀመሩ ሲሆን ፣ ዩኤኢ የዋንግ አራተኛ ማረፊያ ናት፡፡ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ኢራን ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክን ጎብኝተዋል ፡፡ ሲጂቲኤን እንደዘገበው ኦማን እና ባህሬን ደግሞ ቀጣይ ማረፊያው ይሆናሉ፡፡