ቻይና በካናዳ ህግ አውጪና ቤተሰባቸው ላይ ለተቃዋሚዎች "ምሳሌ" የሚሆን እርምጃ ለመውሰድ መረጃ ስትሰበስብ ነበር ተብሏል
የካናዳ ህግ አውጪ አሳዩት በተባለ ጸረ-ቻይና አቋም ቤጂንግና ኦታዎ ውጥረት ውስጥ ገብተዋል።
የቻይና አምባሳደር ኮንግ ፒዩ የቤጂንግ ባለስልጣናት በካናዳ ህግ አውጪ እና ቤተሰባቸው ላይ አነጣጥረዋል መባሉን አስተባብለዋል።
የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ ቤጂንግ አሳየችው በተባለ አቋም "ዲፕሎማቶችን ማባረርን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን እየገመገምን ነው" ብለዋል።
የቻይናን ዲፕሎማት ለማባረር እያጤንኩ ነው ያለውን የኦታዎ መግለጫ አምባሳደር ፒዩ አውግዘዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ኢላማ ሆነዋል የተባሉት ህግ አውጪ በፈረንጆቹ 2021 የወግ አጥባቂ ፓርቲ የፓርላማ አባል ማይክል ቾንግ የቻይናን አናሳ ሙስሊሞች አያያዝን ያሳወቀውን እንቅስቃሴ ደግፈዋል።
የካናዳው ግሎብ ኤንድ ሜል ጋዜጣ የ2021 የካናዳ የስለላ ሪፖርትን በመጥቀስ ቻይና በቾንግ እና ቤተሰባቸው ላይ ለተቃዋሚዎች "ምሳሌ" የሚሆን እርምጃ ለመውሰድ መረጃ ስትሰበስብ ነበር ብሏል።
በካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን የተጠሩት አምባሳደር ኮንግ "የቻይና ጣልቃ-ገብነት" እየተባለ በሚነዛ ወሬ ምክንያት የቤጂንግን ዲፕሎማት ለማባረር ያለውን "ዛቻ" ተቃውመዋል።
ኤምባሲው በድረ-ገጹ በተሰጠ መግለጫ "ቻይና ካናዳ የፖለቲካ ሽኩቻን በአስቸኳይ እንድታቆም አጥብቃ ትጠይቃለች" ብሏል።
መግለጫው አክሎም ካናዳ "ወደ የተሳሳተ እና አደገኛ መንገድ መሄድ የለባትም" ብሏል።