የልጅ ልጁን ጠልፎ 70 ሺህ ዶላር ማስለቀቂያ የጠየቀው ቻይናዊ
ዩዋን የተባለው የ65 አመት ቻይናዊ የ4 አመት የልጅ ልጁን የጠለፈው በቁማር የተበላውን ገንዘብ ለመመለስ ነው ተብሏል
የልጅ ልጁን ጠልፎ ማስለቀቂያ ገንዘብ ከልጁ የጠየቀው አዛውንት ዘብጥያ መውረዱ ተነግሯል
በቻይና የቁማር ሱስ የ65 አመቱን አዛውንት የልጅ ልጁን ጠልፎ ማስመለሻ ገንዘብ እንዲጠይቅ ማድረጉ መነጋገሪያ ሆኗል።
ዩዋን የተባለው ግለሰብ የ4 አመት የልጅ ልጁን ከእናቷ እውቅና ውጭ ምግብ ልግዛልሽ በሚል ሰበብ ከመዋዕለ ህጻናት ይዞ ይወጣል።
እናቷ (የጠላፊው ልጅ) ወደ መዋዕለ ህጻናት ስታመራም ልጇ ከአያቷ ጋር መውጣቷ ይነገራታል።
በሁኔታው ግራ የተጋባችው እናት ከአፍታ በኋላም ከአባቷ መልዕክት ይደርሳታል፤ “የምትሳሽላትን ልጅ ማየት ከፈለግሽ በሶስት ቀናት ውስጥ 72 ሺህ ዶላር (500 ሺህ ዩዋን) መላክ አለብሽ” የሚል።
ስሟ ያልተጠቀሰው የዩዋን ልጅ በአያቷ የተጠለፈችውን ልጇን ለማስለቀቅ አባቷን ለማሳመን ያደረገችው ጥረትም ሳይሳካ ይቀራል።
የመጨረሻ አማራጯም ወደ ፖሊስ መደወል ነበርና ደውላ በእለቱ ማታ ላይ የ65 አመቱ አዛውንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ በሻንጋይ ሺንሹኣ ማረሚያ ቤት ዘብጥያ ወርዷል ይላል የአፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገባ።
ዩዋን ፍርድቤት ሲቀርብ “ጠለፋው የቤተሰብ ጉዳይ ነው፤ ወንጀል አይደለም” ሲል መከራከሩም ተገልጿል።
መረጃውን ቀድሞ ያወጣው የሻንጋይ ጆርናል አዛውንቱ ለምን ያህል ጊዜ በእስር ቤት እንደሚቆይ አልጠቀሰም።
የ65 አመቱ አዛውንት ከፍተኛ የቁማር ሱስ ከሚስቱ እንዳፋታውና ለሆድ ካንሰር እንዳጋለጠው የተገለጸ ሲሆን፥ የልጅ ልጁን ጠልፎ ማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቁ የቁማር ሱስ ምን ያህል በደም ስሩ እንደገባ ያሳያል ተብሏል።
የ4 አመቷን የልጅ ልጁን ጠልፎ በቁማር የተበላውን ገንዘብ ሊመልስ የነበረው ዩዋን የቀድሞ ባለቤቴና ልጄ ካልጠየቁኝ አልበላም ብሎ የረሃብ አድማ ጀምሮ እንደነበር የቻይናው ዘ ፔፐር ጋዜጣ አስነብቧል።
“እንድሻሻል አይፈልጉም፤ እንድሞት ነው የሚፈልጉት” ያላቸው የቀድሞ ባለቤቱና ልጁ በእስርቤት ከጠየቁት በኋላ መመገብ የጀመረው ዩዋን የፈጸመው ድርጊት በቻይናውያን ከፍተኛ ትችት አስከትሎበታል።