ኔቶ የቻይና እና ሩሲያ ጂኦፖለቲካዊ ፈተናዎችን በማሰብ በጃፓን የእስያ የመጀመሪያውን የግንኙነት ቢሮ ለመክፈት ማቀዱ ተነግሯል
ቻይና የኔቶ በእስያ መስፋፋት 'ከፍተኛ ጥንቃቄ' የሚሻ ነው አለች።
ቻይና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በጃፓን ከቀጣናው አጋሮች ጋር የሚመክርበት ቢሮ ለመክፈት ማቀዱን ተከትሎ ጥንቃቄ የሚሻ ነው ብላለች።
ኔቶ "ወደ ምስራቅ መስፋፋት ከፍተኛ ጥንቃቄ" እንደሚያስፈልገው ቤጂንግ ገልጻለች።
ኔቶ እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ካሉ የደህንነት አጋሮች ጋር ውይይት ለማድረግ የቻይና እና ሩሲያ የጂኦፖለቲካዊ ፈተናዎችን በማሰብ በጃፓን የእስያ የመጀመሪያውን የግንኙነት ቢሮ ለመክፈት ማቀዱ ተነግሯል።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ እንዳሉት እስያ "ለመተባበር እና ለልማት ተስፋ ሰጭ ቀጣና ነው። የጂኦ ፖለቲካል ጦርነት አውድማ መሆን የለበትም" ብለዋል።
የኔቶ የምስራቅ እስያ-ፓሲፊክ መስፋፋት በክልላዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባት ፣ ክልላዊ ሰላም እና መረጋጋትን ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራ በመሆኑ ከአካባቢው ሀገራት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግሯል።
የታቀደው የኔቶ ቢሮ በሚቀጥለው ዓመት በቶኪዮ ይከፈታል መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
የኔቶ ቃል አቀባይ ስለታቀደው የቶኪዮ ቢሮ ተጠይቀው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።