በነፍሳት ሴል ዉስጥ የተመረተ አዲስ ክትባትም በሰው ላይ እንዲሞከር ሀገሪቱ ፈቃድ ሰጥታለች
ቻይና የኮቪድ-19 ክትባቶች ለአስቸኳይ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቀደች
በተመረጡ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የተመረቱ የ ኮቪድ-19 ክትባቶች ለአስቸኳይ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ቻይና ፈቃድ መስጠቷን አንድ የሀገሪቱ የጤና ባለሥልጣን ትናንት ቅዳሜ ሐምሌ 22/2012 ዓ.ም ቀን አረጋግጠዋል፡፡
የቻይና የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሃላፊ የሆኑት ዢንግ ዦንግዌይ “የህክምና ስምምነት ቅጾችን ፣ የጎንዮሽ ጉዳቶችን የመቆጣጠር እቅዶችን ፣ የማዳን እቅዶችን ፣ የጉዳት ማካካሻ ዕቅዶችን ጨምሮ የተለያዩ የእቅድ ፓኬጆችን አዘጋጅተናል” ሲሉ ለሲሲቲቪ ተናግረዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ ክትባት እንዲሰጥ የተፈቀደው በሀገሪቱ የክትባት አስተዳደር ህግ ሲሆን ፣ ሙሉ ፈቀድ ያላገኙ ክትባቶችን ለቫይረሱ ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ፣ ግለሰቦች ብቻ ይከተባሉ፡፡
የሙከራ ሂደታቸውን አጠናቀው ፈቃድ ያላገኙ የህክምና ዉጤቶች ከቻይና በተጨማሪ በሌሎችም በርካታ ሀገራት ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ይፈቀዳሉ፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ አደጋዎች (በሽታዎች) በሚከሰቱበት ጊዜ እነዚህን ለመከላከል ፈቃድ ያላገኙ መድኃኒቶች ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የሀገሪቱ ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር እውቅና ሰጥቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው በውድድር በሚካሔዱበት በአሁኑ ወቅት ቻይና አንድ አዲስ የኮሮና ክትባት በሰው ላይ እንዲሞከር ፈቃድ ሰጥታለች፡፡
ሀገሪቱ ፈቃድ የሰጠችው ክትባት በምዕራብ ቻይና በሚገኘው የሲቹዋን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የተመረተ ነው፡፡ ክትባቱ በነፍሳት ሴል ዉስጥ የተመረተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም የነፍሳትን ሴሎች በመጠቀም የኮሮ ቫይረስ ክትባት ፕሮቲኖችን ለማሳደግ በቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ሙከራ ነው፡፡
ክትባቱ በእንስሳት ላይ በተደረገ ሙከራ የኮሮናቫይረስ ኢንፌክሽንን ለመከላከል ጥሩ ውጤት ያሳየ ሲሆን ምንም ግልፅ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳልተገኘበትም ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የቻይና ብሔራዊ የህክምና ዉጤቶች አስተዳደር እንደገለጸው ፣ እስካሁን ስምንት የተለያዩ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች የተለያየ ደረጃ ሙከራ ተደርጎላቸዋል፡፡
እነዚህ ክትባቶች ከ 20,000 በላይ ሰዎች ላይ ተሞክረው ደህንነታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ዉጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ በቅርብ ክትትል እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡