ገንዘቡ ለህክምና ቁሳቁሶች መግዣ እና ብሄራዊ ሃብት አሰባሳቢ ግብረ ኃይሉን ለመደገፍ እንደሚውልም ነው የተገለጸው
በቻይና በትምህርት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ኮሮናን ለመግታት የተጀመረውን ሃገራዊ ጥረት ለማገዝ የሚያስችል ገንዘብ ድጋፍ አደረጉ
የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት በመንግስትና በህዝብ የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ የሚያስችል 452 ሺ 589 ዩዋን (እንደ እለተ ሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2012 ዓ/ም የምንዛሬ ዋጋ 1 ነጥብ 9 ሚሊዬን ብር ገደማ) በቤጂንግ የኢፌዲሪ ኤምባሲ፣በሻንሃይ፣በጓንዦ እና ቾንችን ከተሞች ከሚገኙ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች እንዲሁም በቻይና ከሚማሩ ኢትዮጵያውያን እና የዳያስፖራ አባላት ተሰብስቧል፡፡
ከተማሪዎቹ፣በዳያስፖራ አባላቱና አቶ አስቻለው በላይ በተባሉ የቤጂንግ ነዋሪ በተሰበሰበው 101 ሺ 189 ዩዋን (424 ሺ ብር ገደማ)የህክምና ቁሳቁሶችን ገዝቶ ለመላክ እየተሰራ ነው፡፡
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ቁሳቁሶቹን እያፈላለገ ነው ያለው ኤምባሲው ቀሪው 351 ሺ 400 ዩዋን (1 ነጥብ 4 ሚሊዬን ብር ገደማ) ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለተቋቋመው ብሄራዊ ሃብት አሰባሳቢ ግብረ ኃይል ስለመላኩ አስታውቋል፡፡
በኤምባሲው እያገለገሉ የሚገኙ የኢምግሬሽንና የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ሁለት ሰራተኞች እንዲሁም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባልደረባ የወር ደሞዛቸው በድምሩ 23 ሺ 892 ብር ተቆራጭ ሆኖ በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ እንዲውል ለግሰዋል፡፡
አሁን ከተሰባሰበው ድጋፍ በተጨማሪ ከኤምባሲው፣ከቆንስላ ጽ/ቤቶቹ፣ከተማሪዎችና ከነዋሪዎች የተውጣጡ ግብረ ኃይሎች በቻይና ከተለያዩ የመንግስት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣የግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች ተጨማሪ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማሰባሰብ እየሰሩ እንደሚገኙም ኤምባሲው አስታውቋል፡፡