ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የወደብ ኪራይ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረረማቸውን ተከትሎ ሀገራት አቋማቸውን እየገለጹ ነው
ቻይና ለሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ ኪራይ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ነው ቤጂንግ ለሞቃዲሾ ድጋፏን የገለጸችው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ፥ “ቻይና የመንግስታቱ ድርጅት ቻርተር መርሆዎች እንዲከበሩና የሀገራት ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲጠበቅ ድጋፍ ታደርጋለች” ብለዋል።
ቃል አቀባዩዋ “ሶማሊላንድ የሶማሊያ አካል ናት” ማለታቸውንም አናዶሉ አስነብቧል።
ሞቃዲሾ ሶማሊላንድን የግዛቴ አካል ናት እንደምትለው ሁሉ ቤጂንግም ታይዋንን የሉአላዊ ግዛቷ አካል አድርጋ እንደምትቆጥራት ይታወቃል።
ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በደረሰችው የመግባቢያ ስምምነት የሀገርነት እውቅና ታገኛለች መባሉም የሶማሊያ መንግስትን ማስቆጣቱ ይታወሳል።
ከ1991 ጀምሮ ነጻ ሀገር ሆኛለሁ፤ ምርጫም እያካሄድኩ ነው የምትለው ሶማሊላንድ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ የነጻ ሀገርነት እውቅናን አላገኘችም።
ሶማሊያን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት የሶማሊያን ሉአላዊነትና አለማቀፉን ህግ የጣሰ ነው በሚል ሲቃወሙትና ከሞቃዲሾ ጎን እንደሚቆሙ ሲገልጹ ቆይተዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድም የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነትን የሚሽር ህግ ከመፈረማቸው ባሻገር የሀገራትን ድጋፍ ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ከሶማሌላንድ ላይ የደረስኩት የመግባቢያ ስምምነት የሚጎዳው ሀገርም ሆነ የሚጥሰው ህግ የለም የሚል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ለባህር ኃይል የሚሆን የጦር ሰፈር ስታገኝ፤ ሶማሊላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደምታገኝ በመግለጽም ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና መስጠትን በተመለከተ ኢትዮጵያ አጢና አቋም ትወስዳለች ማለቱ አይዘነጋም።