ሱዳን ስለኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት ምን አለች?
በሁለቱ ጀነራሎች ጦርነት ሰላም የራቃት ካርቱም የሀገራት ሉአላዊነት እና አለማቀፍ ህጎች ሊከበሩ ይገባል ብላለች
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መድረስ ያልቻለችው ግብጽም ተመሳሳይ አቋሟን አንጸባርቃለች
ሱዳን በቅርቡ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የደረሱትን የመግባቢያ ስምምነት አመልክቶ አቋሟን አሳውቃለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሰኞ እለት በአዲስ አበባ የተደረሰውን ስምምነት በአንክሮ እየተከታተልነው ነው ብሏል።
በሁለቱ ጀነራሎች ጦርነት ሰላም ከራቃት ዘጠኝ ወራት ያስቆጠረችው ካርቱም ስምምነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ያሳስበኛል ብላለች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት ማቋቋሚያ ቻርተርና ሌሎች ህግጋት ይከበሩ ዘንድ ጠይቋል።
“በአለማቀፍ ደረጃ እውቅና የተሰጣቸውን የሀገራት ድንበሮችና ሉአላዊነትን ማክበር የአለም ሰላምና ደህንነት መሰረት ነው” ያለው መግለጫው፥ የሀገራት ግንኙነትም በዚህ መሰረታዊ ጉዳይ ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባው ጠቅሷል።
የሀገራት ግንኙነት አለማቀፍ እውቅና ባላቸው መንግስታት እንጂ በሌሎች አካላት እንደማይመሰረት የጠቀሰው መግለጫው፥
ሱዳን በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት “የሶማሊያን ሉአላዊነት ባከበረና አለማቀፉን መርህ ባልጣሰ መልኩ” እንዲፈታ ጥሪ ታቀርባለች ብሏል።
ካርቱም በመግለጫዋ ኢትዮጵያ አለማቀፉ ማህበረሰብ የሀገርነት እውቅና ካልሰጣት ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መድረሷን በገደምዳሜ ተቃውማለች።
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መድረስ ያልቻለችው ግብጽም የሶማሊያን ሉአላዊነት እንደምታከብር መግለጿ ይታወሳል።
ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት የምትላትና ከ32 አመት በፊት ነጻ ሀገር መሆኗን ያወጀችው ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በወደብና ሌሎች ጉዳዮች በትብብር ለመስራት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ መፈረሟ ሞቃዲሾን አበሳጭቷል።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ እውቅና እንድትሰጣት እና በምትኩ 20 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የባህር ጠረፍ ለ50 አመታት እንድከራይ ስምምነት ላይ መደረሱን መግለጹ ነው ሶማሊያን ሉአላዊነቴ ተደፍሯል ያስባላት።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድን ጨምሮ የሀገሪቱ ባለስልጣናትም በበረቱ ቃላት ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን፥ የመንግስታቱ ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ትናንት ባወጣው መግለጫ ግን በስምምነቱ የተጣሰ ህግ የለም በሚል በሶማሊያ መንግስት የሚያቀርበውን ወቀሳ ውድቅ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሶማሊላንድ የበርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ እንዲኖራት የሚፈቅድ የመግባቢያ ሰነድ ስትፈራረም ኮሽታ አልነበረም ያለው መንግስት "ወታራዊ ቤዝ እና የማሪታይም አገልግሎት በሰጥቶ መቀበል እና በከራይ" ለማግኘት የተፈራረመችውም ተመሳሳይ ነው ብሏል።