የዋሽንግተን ፖለቲከኞች በበኩላቸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የቻይና ጉብኝታቸውን እንዲሰርዙ ጠይቀዋል
ቻይና ተንሳፋፊ ፊኛን በመጠቀም አሜሪካን እና ካናዳን መሰለሏ ተገለጸ።
ባለፉት ሁለት ቀናት የቻይና ንብረት የሆኑ የስለላ ተንሳፋፊ ፊኛዎች በአሜሪካ ከተሞች ላይ ሲበሩ መታየታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዋሽንግተን ፊኛዎቹን ለመቆጣጠር ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖችን ለማሰማራት አስባ ነበር የተባለ ሲሆን የነጩ ቤተመንግስት ግን ፊኛዎቹ ቢመቱ በሰዎች ላይ አደጋ ሊያደርስ የሚችሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል እቅዱ ሳይፈጸም ቀርቷል ተብሏል።
- ቻይና፤ አሜሪካን “የማጥፋትም ሆነ የመተካት አላማ” እንደሌላት የቻይና ዲፕሎማት ተናገሩ
- ቻይና፤ አሜሪካ ጸብ አጫሪ ድርጊት ከፈጸመች ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቷን ገለጸች
እነዚህ ተንሳፋፊ ፊኛዎችም የአሜሪካ ከተሞችን አልፈው ወደ ካናዳ የአየር ክልል እንደገቡም ተገልጿል።
ፊኛዎቹ የአሜሪካንን የአየር ክልል ጥሰው ከገቡበት ጊዜ ጀምሮም ሁኔታውን እየተከታተለች እንደሆነም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ክስተቱ ቻይና በአሜሪካ ላይ የሰነዘረችው ጥቃት አካል ነው ያለችው አሜሪካ ጉዳዩ እንዳሳሰባት አስታውቃለች። የአሜሪካ ስለላ ድርጅት ሲአኤ ሀላፊ የሆኑት ዊሊያም በርንስ በበኩላቸው ቻይና የአሜሪካ ዋነኛ ስጋት ናት ብለዋል።
የአሜሪካ ፖለቲከኞች በድርጊቱ መበሳጨታቸውን በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ሲሆን አሜሪካ እርምጃ እንድትወስድ በመወትወት ላይ ናቸው።
የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ አንቶኒ ብሊንከን በነገው ዕለት ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ቤጂንግ እንደሚጓዙ ይጠበቃል። ይሁንና የአንቶኒ ብሊንከን ጉብኝት እንዲሰረዝ የአሜሪካ ሴናተሮች በተለያዩ መንገዶች ጠይቀዋል።
በአሜሪካ በተንሳፋፊ ፊኛ ተሰልያለሁ በሚል ክስ የቀረበባት ቻይና በበኩሏ እስካሁን ስለጉዳዩ ያለችው ነገር የለም።