ቻይና፤ አሜሪካ ጸብ አጫሪ ድርጊት ከፈጸመች ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቷን ገለጸች
ቤጅንግ፤ ከዋሸንግተን ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር ማቋረጧን መግለጿ ይታወሳል
የፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ከፍተኛ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል
ቻይና፤ አሜሪካ ከዚህ በኋላ ጸብ አጫሪ ድርጊት ከፈጸመች ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀቷን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ ዋሸንግተን በቻይና ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያነጣጠረ ጸብ አጫሪ ድርጊት ከፈጸመች እንደማይታገስ ገልጿል፡፡ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ዛሬ በመግለጫቸው አሜሪካ፤ ቻይናን ለመያዝ ታይዋንን ከመጠቀም እንድትቆጠብ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
የቻይና ባለስልጣናት አሜሪካ ፤ ታይዋንን በመጠቀም፣ የቤጅንግ ብሔራዊ ጥቅም እየጎዳች መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለጹ ናቸው፡፡ ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢንም ይህንኑ ሃሳብ በዛሬ ድጋሚ አንስተውታል፡፡ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፤ የናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ጸብ አጫሪ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ በኋላ ግን ለጸብ የሚያነሳሳ ድርጊት ከዋሸንግተን ከመጣ ቻይና አጸፋውን ለመመለስ መዘጋጀቷን ተናግረዋል፡፡
ቻይና ከአሜሪካ ጋር የነበራትን ወታደራዊ ትብብር ማቋረጧን ተከትሎ ዋሸንግተን ድርጊቱን አውግዛ ነበር፡፡ ቤጅንግ ግን ሁሉንም እርምጃዎች የወሰደችው አሜሪካ ጸብ አጫሪ ድርጊትን ከፈጸመች በኋላ በመሆኑ የወሰደቻቸው እርምጃዎች ሚዛዊና ትክክል መሆናቸውን ገልጻለች፡፡
ቻይና እና ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ትብብርን ጨምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያም ንግግርና ውይይት የነበራት ቢሆንም በፔሎሲ ጉብኝት ምክንያት ሁሉንም ላለማድረግ ውሳኔ ማሳለፏን ማሳወቋ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም የፕሬዝዳንት ዢ ሺን ፒንግ አስተዳደር፤ ሀገሪቱ ከአሜሪካ ጋር የነበራትን የድንበር አልባ ወንጀል መከላከል፣ ስደተኞችን የማጓጓዝ፣ አደገኛ ዕጽ ዝውውር መከላከል እና ሌሎች ስምንት የትብብር መስኮችን ማቋረጡን ገልጿል፡፡
ቻይናና አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበላይነትን ለማስፈን ከሚደረግ ሽኩቻ ባለፈ በንግድና ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ እሰጥ አገባ የነበራቸው ቢሆንም ታይዋን ግን የሀገራቱን ግብ ግብ የበለጠ እንዲካረር አድርጋዋለች ተብሏል፡፡