አሜሪካን መምታት ይችላሉ የተባሉት የሰሜን ኮሪያ ሚሳዔሎች የትኞቹ ናቸው…?
“ሃውሶንግ”አህጉር አቋራጭ ሚሳዔሎች ከ4 ሺህ እስከ 15 ሺህ ኪሎ ሜትር ድረስ ማጥቃት ይችላሉ
ሰሜን ኮሪያ ከሰሞኑ አሜሪካ ላይ “ከባድ ወታደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ” በማለት ዝታለች
ፒዮንግ ያንግ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን በካምቦዲያ ካደረጉት የሶስትዮሽ ስብሰባ በኋላ ቁጣዋን ለመግለጽ ሚሳዔሎችን እያስወነጨፈች መሆኑ ይታወቃል።
ሰሜን ኮሪያ “የኮሪያ ልሳነ ምድርን እያወከች ነው” ባለቻት አሜሪካ ላይ ከባድ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ሰሜን ኮሪያ በትናትናው እለትም አሜሪካ መድረስ የሚችል ባለስቲክ ሚሳኤል ወደ ጃፓን ያስወነጨፈች ሲሆን፤ የባለስቲክ ሚሳኤሉ 1 ሺህ ኪሎሜትሮችን መጓዙ ተነግሯል።
አሜሪካን መምታት ይችላሉ የተባሉት የሰሜን ኮሪያ ሚሳዔሎች የትኞቹ ናቸው?
ሰሜን ኮሪያ ባለንበት የፈረንጆቹ 2022 ብቻ በርካታ የሚሳዔል ማስወንጨፍ ሙከራዎችን ያደረገች ሲሆን፤ አሜሪካን መምታት የሚችሉንትን የረጅም ርቀት ሚሳዔል ጨምሮ እስከ አጭር ርቀት ሚሳዔል ድረስ ሙከራዎችን አድርጋለች።
ሀገሪቱ ሙከራ ያደረገችባቸው የሚሳዔል አይነቶችም ውስጥም ባላስቲክ ሚሳዔል፣ ክሩዝ ሚሳዔል እና ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል ይገኙበታል።
ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔል የራዳር ቁጥጥርን መጣስ የሚችል እና ከድምጽ በብዙ እጥፍ የሚፈጥን የመሳሪያ አይነት መሆኑ ይታወቃል።
ከእነዚህም ውስጥ አሜሪካን መምታት የችላ የተባሉት “ሃውሶንግ” የሚል መጠሪያ ላቸው የሚሳዔል አይነቶች ተጠቃሽ ናቸው።
ሃውሶንግ ሚሳዔሎችም የተለያዩ ርቀት የሚጓዙ የሚሳዔል አይነቶች ያሏቸው ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ “ሃውሶንግ-12” አንዱ ሲሆን፤ እስከ 4 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር መጓ የሚችል ነው።
“ሃውሶንግ-14” የሚባለው ሚሳዔል 10 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር፣ “ሃውሶንግ-15” እስክ 13 ሺህ ኪሎ ሜትር እንዲሁም “ሃውሶንግ-17” ከ15 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ጥቃት መፈጸም የሚችሉ ናቸው።
ለአብነትም ሃውሶንግ-14 የሚል መጠሪያ ያለው አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳኤሎች ከ8 ሺህ እሰከ 10 ሺህ ኪሎ ሜትር ድረስ ማጥቃት የሚችል ሲሆን፤ ይህም የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማን የመምታት አቅም ያለው መሆኑን ከጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር ሲ.ኤስ.አይ የሚሳዔል መከላከያ ፕሮጅከት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።