ቻይና፤ አሜሪካን “የማጥፋትም ሆነ የመተካት አላማ” እንደሌላት የቻይና ዲፕሎማት ተናገሩ
ቤጅንግ የራሷን ደህንነቷን ለማረጋገጥ በሚል ሌሎችን አደጋ ላይ እንደማትጥልም ገልጻለች
ዲፕሎማቱ፤ ከ “ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ጦርነት ምን ትማራላችሁ” ተብለው ሲጠየቁ “አሜሪካ፤ ከዩክሬን ግጭት ምን እንደተማረች አላውቅም” ሲሉ መልሰዋል
በአሜሪካ የቻይና አምባሳደር፤ ቤጅንግ ዋሸንግተንን የመተካት ወይንም የማጥፋት ዕቅድ እንደሌላት አስታወቁ፡፡
አምባሳደር ኪን ጋንግ ይህንን አስተያየት የሰጡት በአሜሪካ ከሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው፡፡
የአሜሪካ ፖለቲከኞች ቻይናን በተመለከተ ያላቸው አቋም ችግር ያለበትና የተጣመመ ነው ያሉት ዲፕሎማቱ፤ ሀገራቸው ግን ስጋት ልትሆን አትችልም ብለዋል፡፡ “እኔ እዚህ ሀገር አምባሳደር ነኝ፤ እዚህ ሀገር ሀገሬን ያለ አግባብ በስህተት ሲያብጠለጥሉ እሰማለሁ ሲሉም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት፡፡
ቻይና ስጋትም ሆነ ፈተና እንደማትሆን የተናገሩት አምባሳደሩ፤ የቤጅንግ ዋነኛ ዓላማ ሕዝብ የተሻለ ነገርን እንዲያገኝ ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ቻይና፤ አሜሪካን የማጥፋትም ሆነ የመተካት አላማ እንደሌላትም ለጋዜጠኞቹ ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ ለሚፈጠር እያንዳንዱ ችግር ቻይናን ተጠያቂ ማድረግና በቻይና ማሳበብ ተገቢ እንዳልሆነም ነው አምባሳደር ኪን የተናገሩት፡፡ ቻይናን ስጋት አድርገው ያስባሉ ያሏቸው የአሜሪካ ፖለቲከኞች ከዚህ አይነት የተሳሳተ አረዳድ ሊወጡ እንደሚገባ ዲፕሎማቱ ተናግረዋል፡፡
ዲፕሎማቱ፤ በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ልዩነት እንዳለ ቢታወቅም፤ ልዩነቶችን መነሻ በማድረግ ግን ያልሆነ ወቀሳና ፍረጃ ውስጥ መገባት የለበትም ብለዋል፡፡ በሀገራቱ መካከል ያሉትን ልዩነቶች የግንኙነት መነሻ ማድረግ አስፈላጊ እንዳልሆነም ዲፕሎማቱ አንስተዋል፡፡
ዲፕሎማቱ ቆይታ ካደረጉባቸው መገናኛ ብዙኃን መካከል የአሜሪካው ናሽናል ፐብሊክ ራዲዮ “ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረችበት ጦርነት ቻይና ምን ትማራለች” የሚል አቅርቦላቸውም ነበር፡፡ ዲፕሎማቱም “አሜሪካ ከዩክሬን ግጭት ምን ልትማር እንደምትችል አላውቅም” ሲሉ መልሰዋል፡፡ ቤጅንግ ፤ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከመከሰቱ አስቀድሞ ችግሩ በሰላም ይፈታ የሚል አቋም ስታራምድ እንደቆየችም ነው የገለጹት፡፡
ቻይና፤ ማንኛውም ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ሁልጊዜም ጽኑ አቋ እንዳላት ያለሱት ዲፕሎማቱ ኔቶም ሆነ አሜሪካ ከዩክሬን ቀውስ መማር እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡ ቤጅንግ የራሷን ጸጥታና ሰላም ለማረጋገጥ ብላ የሌሎችን ደህንነት አደጋ ላይ አትጥልምም ብለዋል፡፡
በዶናልድ ትራምፕ ዘመን ቻይናና አሜሪካ በኢኮኖሚ ውጥረት ውስጥ የነበሩ ሲሆን አሁን ደግሞ የሀገራቱ የግጭትና ውጥረት መንስዔ ታይዋን ሆናለች፡፡