ቻይና ለ6 እና 7 ዓመት ልጆች የጽሁፍ ፈተና እና የቤት ሥራ እንዳይሰጥ አገደች
ውሳኔው በቻይና የትምህርት ዘርፍ እየተወሰደ ያለው ሰፊ የማሻሻያ አካል ነው ተብሏል
የሚኒስቴሩ እርምጃው በህጻናት ላይ ያለውን ጫና ይቀንሳል የሚሉ እንዳሉ ሁላ ያለፈተና የተማሪዎችን እውቀት እንዴት መመዘን ይቻላል በማለት የሚጠይቁም አሉ
እገዳው ውድድር በበዛበት የትምህርት ሥርዓት ውስጥ በተማሪዎችና በወላጆች ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለማቃለል የተወሰደ እርምጃ ነው ተብሏል።
ውሳኔው በቻይና የትምህርት ዘርፍ እየተወሰደ ያለው ሰፊ የማሻሻያ አካል መሆኑንም ነው ኤኤፍፒ የዘገበው።ከዚህ ቀደም ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከገቡ ከመጀመሪያው ዓመት አንስቶ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና እስከሚወስዱበት 18 ዓመታቸው ድረስ ፈተና መውሰድ ይጠበቅባቸው ነበር።
ነገር ግን ይህ ጫና የተማሪዎቹን "አካላዊና አዕምሯዊ ጤናን" እየጎዳ መሆኑን የቻይና ትምህርት ሚኒሰቴር ገልጿል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው "ፈተናዎች የትምህርት ቤት ሥርዓት አካል ሲሆኑ አስፈላጊ ናቸው፤ ነገር ግን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በርካታ ፈተና ይሰጣሉ፡፡ ይህም በልጆቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ይፈጥራል። በመሆኑም መስተካከል አለበት" ብሏል።
መመሪያው አንድ ትምህርት ቤት በአንድ ሰሚስቴር ሊያዘጋጃቸው የሚችሉ የፈተናዎች ብዛትንም ይገድባል።
"የአንደኛ እና የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ጽሁፍ ላይ የተመሰረተ ፈተና መውሰድ አይጠበቅባቸውም። በሌሎች ክፍሎች ግን ትምህርት ቤቶች በየወሰነ ትምህርቱ ማጠቃለያ ላይ ፈተና መስጠት ይችላሉ። ለመካከለኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በየወሰነ ትምህርቱ ማጠቃለያ እና አጋማሽ ፈተናዎችን መስጠት ይፈቀዳል" ብሏል ሚኒስቴሩ።
ከዚህም በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ለሁሉም የአንደኛ ደረጃ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ አሊያም የመግቢያ ፈተና መስጠት እንደማይፈቀድ ገልጿል።
ያልተመረቁ የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሳምንታዊ፣ የትምህርት ማጠቃለያ እና ወርሃዊ ፈተናዎች መውሰድ አይጠበቅባቸውም ብሏል ሚኒሰቴሩ፡፡ይህ ብቻም ሳይሆን 'ትምህርታዊ ምርምር' በሚል ሌላ ስያሜ የሚሰጡ ፈተናዎችም አይፈቀዱም።
በዚህ መመሪያ ላይ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ 'ዌቦ' ተጠቃሚዎች የተለያዩ ሃሳቦችን እያንፀባረቁ ነው።
አንዳንዶች በህጻናት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመጓዝ የሚያስችል አንድ እርምጃ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ በተቃራኒ ትምህርት ቤቶች ያለ ፈተና የተማሪዎችን ችሎታ እና እውቀት እንዴት መመዘን ይችላሉ ሲሉ ይጠይቃሉ። የቻይና የትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዓመት ለአንደኛ ክፍል ተማሪዎች የቤት ሥራ እንዳይሰጥም አግዷል፡፡