የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ቱኒዚያ ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድርን በማስቀጠል ከስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ ነች- አቶ ደመቀ መኮንን
የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ዳግም በቱኒዚያ በኩል ወደ ምክር ቤቱ መቅረቡ ተገቢ አይደለም- ዶ/ር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት አምባሳደሮችን አነጋግረዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በቱኒዚያ አማካይነት የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ እንዲደረግ ወቅት ጥሪ ማቅረባቸውን አል ዐይን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገነኘው መረጃ ያመለክታል።
አቶ ደመቀ መኮንን አክለውም፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድርን በማስቀጠል ከስምምነት ላይ እንዲደረስ ቁርጠኛ መሆኗንም አስገንዝበዋል።
በቱኒዚያ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ምክር ቤቱ እንዳያሳልፈው አምባሳደሮቹ ለየሀገሮቻቸው መልዕክቱን እንዲያስተላልፉ ጠይቀዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው የአባይን ውሃ አጠቃላይ መረጃ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የግንባታ ደረጃ እና የግድቡ ጠቀሜታን፤ በቱኒዚያ አማካይነት ለተ.መ.ድ የጸጥታው ምክር ቤት የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ይዘት በተመለከተ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያን አቋምን አስመልክቶ ለአምባሳደሮቹ ገለጻ ሰጥተዋል።
ዶ/ር ኢንጅነር ስለሽ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የልማት ፕሮጀክት በመሆኑ በጸጥታው ምክር ቤት መታየት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
አያያዘውም ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ. በጁላይ 2021 ጉዳዩ ለጸጥታው ምክር ቤት ቀርቦ፤ ሶስቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደውን የሶትስትዮሽ ድርድር በማስቀጠል መፍትሔ ላይ እንዲደርሱ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ጉዳዩ ዳግም በቱኒዚያ በኩል ወደ ምክር ቤቱ መቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በቱኒዚያ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብት የሚጋፋ እና ኢ-ፍትሃዊ የሆነውን የታችኞቹን የተፋሰሱ ሀገራት ጥቅም ብቻ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
ሱዳንና ግብጽ ጉዳዩን ፖለቲካዊና አለም አቀፋዊ ከማድረግ ይልቅ በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲሳተፉ እንዲሁም የናይል አጠቃላይ ስምምነት ማዕቀፍን እንዲፈርሙ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
አያይዘውም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሶስትዮሽ ድርድሩን በማስቀጠል የሶስቱን አገሮች ሃሳብ በማካተት ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንዲደረስ በዝግጅት ላይ መሆኗን ጠቁመዋል።