ህንዳውያኑ ጥንዶች አይፎን ለመግዛት የ8 ወር ልጃቸውን ሽጠዋል
በምዕራብ ቤንጋል የሚኖሩት ጥንዶች የኢንስታግራም ቪዲዮዎችን ለመስራት ነው ልጃቸውን የሸጡት
አይፎን ለመግዛት ኩላሊቱን የሸጠ ቻይናዊ ህይወቱን አደጋ ላይ መጣሉ ይታወሳል
የአይፎን ስልክ ለመግዛት የ8 ወር ህጻን ልጃቸውን ለገበያ ያዋሉት ህንዳውያን በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ጃይደን እና ሳትሂ ግሆሽ የተባሉት ጥንዶች በምዕራብ ቤንጋል ግዛት ነዋሪ ናቸው።
ከወለደ አንጀት የማይጠበቅ ተግባራቸው ባለፈው ሳምንት የመላው ህንድ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኗል።
አነስተኛ ገቢ ያላቸውና ሁሌም ከጎረቤት እና ወዳጆቻቸው ብድር በመጠየቅ የሚታወቁት ጥንዶች የአይፎን 14 ስልክ ይዘው እዩልኝ ማብዛታቸው በጎረቤቶቻቸው ምን ተፈጠረ? የሚል ጥርጣሬን ያጭራል።
የ8 ወር ልጃቸው ከእይታ መሰወርም ጥርጣሬያቸውን አንድ ደረጃ ከፍ ያደርገውና ይጠይቋቸዋል፤ ጃይደን እንዳ ሳትሂ ግን ምንም ቁብ ሳይሰጡ በአዲሱ ስልካቸው ቪዲዮዎችን መቅረጽን ይያያዙታል።
በሁኔታው ስጋት የገባቸው ጎረቤቶቻቸው የጥንዶቹ የ8 ወር ህጻን ልጅ መጥፋትን ለፖሊስ ያመለክታሉ።
የአይፎን ስልክ ፍቅራቸው ያልወጣላቸው ጥንዶች በቁጥጥር ስር ውለው ሲጠይቁም በቤንጋል የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወርን የኢንስታግራም ቪዲዮዎችን ለመቅረጽ ስንል ልጃችን ሽጠነዋል ማለታቸውን ኢንዲያን ኤክስፕረስ አስነብቧል።
የያዙት አይፎን 14 አዲስ ስልክም ልጃቸውን ሽጠው ባገኙት ገንዘብ የተገዛ ስለመሆኑ ያለሃፍረት መናገራቸውን ነው ዘገባው ያነሳው።
ፖሊስ ህጻኑን የገዛችውን ፕሪያንካ ጊሆሽ የተሰኘች የካርዳህ ከተማ ነዋሪም በቁጥጥር ስር አውሎ ክስ እንደመሰረተባት ተነግሯል።
ጃይደን እና ሳትሂ ግሆሽ የ7 አመት ታዳጊ ልጃቸውንም ለመሸጥ ሞክረው ሳይሳካላቸው መቅረቱ የተገለጸ ሲሆን፥ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ሰዎች የጓጉለትን ነገር ለማድረግ ወይንም በአለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ለመሆን ያልተገቡ ነገሮችን ሲፈጽሙ ይታያል።
በ2011 ታዋቂ የነበረውን አይፎን 4 ስልክ ለመግዛት አንድ ኩላሊቱን የሸጠው የ17 አመት ቻይናዊ የደረሰበት ጉዳት ለዚህ ማሳያ ነው።
ሺዎ ዋንግ የተባለው ግለሰብ ስልኩን ለመግዛት አንድ ኩላሊቱን ቢሸጥ ምንም እንደማይሆን ቢነገረውም ከቀዶ ጥገናው በኋላ ግን በየቀኑ የኩላሊት እጥበት ማድረግ ግድ እንዲለው ማድረጉ አይዘነጋም።