የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባይደን ሜዳሊያ ሸለሙ
ዘለንስኪ ስጦታውን ያበረከቱት አሜሪካ ለዩክሬን የ1 ነጥብ 85 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ ቃል ከገባች በኋላ ነው
ፕሬዝዳንቱ ስጦታውን የሰጡት አንድን ወታደር ወክለው መሆኑን ተናግረዋል
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አንድ የዩክሬን ወታደርን ወክለው ለአሜሪካ አቻቸው ጆ ባይደን ሜዳሊያ አበርክተዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በትናንትናው እለት በሚስጢር ወደ ዋሽንግተን ያቀኑ ሲሆን ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በመወያየት ላይ ናቸው።
ዘለንስኪ በዋይት ሀውስ ሲናገሩ “የባክሙት” ሰው ወታደራዊ ሜዳሊያውን ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት እንዲሰጡ እንደጠየቁት አስረድተዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን “የማይገባ፤ ግን በጣም እናመሰግናለን” ሲሉ ስለ ስጦታው ምላሽ ሰጥተዋል።
- አሜሪካ ለዩክሬን የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ እንደምትሰጥ ገለጸች
- ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ በጦርነት ከምትታመሰው ዩክሬን እንዴት ሾልከው ወደ አሜሪካ ሊሄዱ ቻሉ?
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አርማ የታተመበት ልዩ ሳንቲም ወደ ወታደሩ ይዘው እንዲመለሱም ባይደን ጠይቀዋቸዋል።
በዋይት ሀውስ መገኘት ትልቅ ክብር ነው በማለት ዘለንስኪ ፕሬዝዳንት ባይደን እና የአሜሪካ ህዝብ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
"ከእኛ ተራ ሰዎች ለእናንተ ተራ ሰዎችዎ፤ አሜሪካውያን እናመሰግናለን" ብለዋል።
"እናመሰግናለን ስንል የምንናገረውን ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ይመስለኛል፤ እዚህ መሆን ትልቅ ክብር ነው" በማለትም ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አክለዋል።
ይህ የሆነው አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ 1 ነጥብ 85 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ እንደምትሰጥ ካወጀች በኋላ ነው። እርዳታው የአየር መከላከያ ስርዓትን ማስተላለፍን ጨምሮ መሆኑን መገናኛ ብዙኸን እየተቀባበሉት ነው።
ዩክሬን የአየር መከላከያ ስርዓቱ የሩሲያን ሚሳይልና የድሮን ጥቃቶችን ለመቋቋም እንዲሰጣት ስትወተውት ቆይታለች።
የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለስልጣናት በድብቅ ባሳለፍነው ሳምንት ያቀናጁት ጉብኝት ከባድ ስጋት እንደፈጠረ ሲኤንኤን ዘግቧል።
ዘለንስኪ በባቡር ፖላንድ ከደረሱ በኋላ በአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ተሳፍረው ወደ ዋሽንግተን እንደበረሩ የአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል።