ቻይና በታይዋን ዙሪያ በ125 የጦር አውሮፕላኖች ግዙፍ ወታራዊ ልምምድ አደረገች
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ይህ ልምምድ የተካሄደው የታይዋን ፕሬዝደንት ላሰሙት ንግግር ምላሽ ነው
ታይዋን ቻይና "የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት የሚሸረሽር ወታደራዊ ትንኮሳ" እንድታቆም ጥሪ አቅርባለች
ቻይና በታይዋን ዙሪያ በ125 የጦር አውሮፕላኖች ግዙፍ ወታራዊ ልምምድ አደረገች።
ቻይና 125 የጦር አውሮፕላኖችን፣ ላይዮኒንግ የተባለችውን የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቧን እና መርከቦችን በመጠቀም በታይዋን ዙሪያ ክብ በመስራት ግዙፍ የተባለ የጦር ልምምድ ማድረጓን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ይህ ልምምድ የተካሄደው ራስ ገዟ ታይዋን የቻይና አካል መሆኗን አልቀበልም ላሉት የታይዋን ፕሬዝደንት ምላሽ ነው።
የታይዋን ብሔራዊ መከላከያ የጦር አውሮፕላኖችን፣ ሄሊኮፕተሮችን እና ድሮኖችን ጨምሮ ከጦር ጄቶቹ 90ዎቹ በታይዋን የአየር መከላከያ መለያ ቀጠና ታይተዋል ብሏል።
ይህ ልምምድ የተካሄደው ታይዋን መንግስት የመሰረተችበትን ቀን ካከበረች ከአራት ቀን በኋላ ነው። በዚህ በዓል ላይ የተገኙት የታይዋን ፕሬዝደንት ላይ ችንግ-ቴ ባሰሙት ንግግር ቻይና ታይዋንን ለመወከል መብት እንደሌላት እና ታይዋንን "የመጠቅለል ወይም የመጣስ" እንቅስቃሴዎችን ለመታገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
"ጦራችን ከቻይና የሚመጣውን ጥቃት በአግባቡ ይመክተዋል" ሲሉ የታይዋን የደህንነት ምክርቤት ዋና ጸኃፊ ጆሴፍ ዉ ተናግረዋል። "ሀገራችንን በኃይል ማስፈራራት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚለውን የተመድን ህግ ይጥሳል።"
የታይዋን ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ቻይና "የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት የሚሸረሽር ወታደራዊ ትንኮሳ እና የታይዋንን ዲሞክራሲ እና ነጻነት የማጥፋት እንቅስቃሴ እንድታቆም" ጥሪ አቅርቧል።
የቻይና ሲሲሲ ቲቪ ልምምድ እየተካደ የሚገኝባቸውን በታይዋን ዙሪያ ያሉ ስድስት ቦታዎች አሳይቷል። የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ስድስቱ ቦታዎች በታይዋን እና በዙሪያዋ ባሉ ስትራተጂካዊ ቦታዎች ላይ ትኩረት አድርገዋል።
የቻይና ጦር ምስራቃዊ ቲያትር ኮማንድ ቃል አቀባይ ከፍተኛ ካፒቴን ሊ ዢ ልምምዱ በስኬት መጠናቀቁን በዛሬው እለት ተናግረዋል። ሊ እንዳሉት ባህር ኃይል፣ አየር ኃይል እና የሚሳይል ቡድኑ በጋራ በመሆን ነው ልምሞዱን ያደረጉት። ሊ በሰጡት መግለጫ "ይህ የታይዋንን ነጻነት ለሚደግፉት ኃይሎች ትልቅ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ እና ቻይና ሉአላዊነቷን ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆኗን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ ቻይና ከታይዋን የሚደረግን ግንኙነት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አድርጋ እንደማታየው እና የታይዋን ነጻነት የማይታሰብ መሆኑን ገልጸዋል።