አሜሪካ የሚሳኤል መቃዎሚያዎችን እና ወታዳሮችን ወደ እስራኤል ልትልክ መሆኑን አስታወቀች
ጦሩ በእስራኤል የሚሰፍረው እስራኤልን ለመደገፍ ፣ ከኢራን ከምትደግፋቸው ቡድኖች ሊፈጽሟቸው ከሚችሉ ጥቃቶች ለመከላከል ነው ተብሏል

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለጉዳዩ በሰጠው ምላሽ ህዝባችንን እና ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ምንም አይነት ቀይ መስመር የለንም ብሏል
አሜሪካ ዘመናዊ የተባለ የሚሳኤል መከላከያ ስርአት እና ወታደሮቿን ወደ እስራኤል ልትልክ መሆኑን የሀገሪቱ መከላከያ ሚንስትር መስርያቤት ፔንታጎን አስታወቅ፡፡
ያልተለመደ ነው በተባለው የጦር ሰፈራ አሜሪካ ከዚህ ቀደም በእስራኤል አቅራቢያ በሚገኙ የውሀ ክፍሎች ካሰፈረቻቸው ወታደሮች በተጨማሪ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከ13 ቀናት በፊት የሄዝቦላህ መሪ የሀሰን ናስረላህ ግድያን ተከትሎ ኢራን በእስራኤል ከ180 በላይ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን ተከትሎ ቴልአቪቭ እወስደዋለሁ ያለቸው ድንገተኛ የበቀል እርምጃ እየተጠበቀ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም ከእስራኤል የአጸፋ ምላሽ በኋላ ምን ሊፈጠር ይችላል በሚል ቀጠናው በከፍተኛ ስጋት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ አሜሪካ ወደ እስራኤል እልካቸዋለሁ ያለቻቸው ወታደሮች በአጻፍ ምላሹ ላይ እገዛ የሚሰጡ እንደሆኑ እና እንዳልሆኑ የታወቀ ነገር አለመኖሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ ጦር ከቅርብ ወራት ወዲህ በአካባቢው ሰፊ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን እስራኤል በኢራን የተፈጸመባትን ጥቃት ለመከላከል ከጦር መርከቦች እና ከጦር ጄቶች ላይ በመሆን ሚሳኤሎችን ለማክሸፍ አግዟል፡፡
ሆኖም ጦሩ በድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ስፍራዎች ከመስፈር እና አልፎ አልፎ ሁለቱ ሀገራት በሚያደርጉት የጦር ልምምድ በእስራኤል ድንበር ውስጥ ከመንቀሳቀስ ባለፈ በእስራኤል ሰፍሮ አያውቅም፡፡
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሜጀር ጄነራል ፓትሪክ ራይደር ጦሩ በእስራኤል የሚሰፍረው አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ባደረገችው የድንበር አሰፋፈር ማሻሻያ መሰረት በቀጠናው የሚገኝውን ጦሯን እንዲሁም እስራኤልን ከኢራን እና በአካባቢው ከሚገኙ ቡድኖች ጥቃት ለመከላከል ነው ብለዋል፡፡
“ተርሚናል ሃይ አልቲቲዩድ ዲፌንስ ሲስተም” (THAAD) የተባለው አሜሪካ ወደ እስራኤል ትልከዋለች የተባለው እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከታጠቁ አሜሪካ ሰራሽ የአየር መቃወሚያዎች መካከል አንዱ ሲሆን መሳርያውን ጥቅም ላይ ለማዋል 100 የሚደርሱ ወታደሮችን ይፈልጋል፡፡
ሎክሂድ ማርቲንበተበለ የጦር መሳርያ አምራች ኩባንያ የተመረተው የሚሳኤል መቃወሚያ የረጅም የአጭር እና የመካከለኛ ርቀት ሚሳኤሎቸን መከላከል የሚችል ነው፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራክቺ አሜሪካ ጦሯን ወደ እስራኤል በመላክ በቀጠናው ሰፍረው የሚገኙ ወታደሮቿን ህይወት አደጋ ውስጥ እየከተተች ነው ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ ባሰፈረት ጽሁፍ “ምንም እንኳን በቀጠናው ሁሉን አቀፍ ጦርነት እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ቢሆንም ህዝባችንን እና ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ምንም አይነት ቀይ መስመር እንደሌለን በግልጽ ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲሉ ጽፈዋል፡፡
ዋሽንግተን የቴል አቪቭ የበቀል እርምጃ በቀጠናው የሚያቀጣጥለውን ግጭት ለመቀነስ እስራኤል ኢላማዋን እንድታስተካከል በግሏ በመማጸን ላይ ላይ ትገኛለች፡፡
ከዚህ ባለፈም በኢራን የኒውክሌር ማብላያ ጣብያዎች ላይ እና በነዳጅ ማውጫ ስፍራዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም በይፋ እየተቃወመች ነው፡፡