ስዊድን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሰራዊት በአውሮፓ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ጠየቀች
ኢራን በስዊድን ያሉ ወሮበሎችን በመቅጠር በስካንድቪዲያን ሀገራት ያሉ የእስራኤል ጥቅሞችን ለመጉዳት እየጣረች ነው ተብሏል
ኢራን በበኩሏ በስዊድን የቀረበባትን ክስ ውድቅ አድርጋለች
ስዊድን የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሰራዊት በአውሮፓ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ጠየቀች።
የስዊድን ጠቅላይ ሚንስትር ኡልፍ ክሪስቴርሴን የአውሮፓ ህብረት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጦርን በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ጥሪ አቅርበዋል።
ለአውሮፓ ህብረት ጥሪውን ያቀረቡት የስዊድኑ ጠቅላይ ሚንስትር ኢራን ስዊድንን ጨምሮ በአውሮፓ በሚገኙ የእስራኤል ኢምባሲዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ በጥረት ላይ ናትም ብለዋል።
በስዊድን የሚገኙ የወንጀለኞችን ቡድንን በመቅጠር በስቶኮልም እና ኮፐንሀገን ባሉ የእስራኤል ኢምባሲዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ እየሞከሩ እንደሆነ ተገልጿል።
ከእስራኤል ኢምባሲ ባለፈ በአውሮፓ የሚገኙ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ኩባንያዎች የጥቃት ኢላማ እየተደረጉ ነውም ተብሏል።
የአውሮፓ ህብረት እስካሁን በስዊድን ጠቅላይ ሚንስትር ስለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ባሳለፍነው ሳምንት የሊቱኒያ ህግ አውጪ ምክር ቤት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጦር በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ውሳኔ አስተላልፏል።
የኢራን መንግሥት በበኩሉ በአውሮፓ የሽብር ጥቃት ለመክፈት እየተንቀሳቀሰ ነው በሚል የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
የኢራን አብዮታዊ ጦር በአሜሪካ እና ካናዳ በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል።
በ1979 የተቋቋመው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጦር ተጠሪነቱ ለሀገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ካሚኒ እና ለኢራን መከላከያ ነው።
ይህ የኢራን አብዮት ጠባቂ ጦር ሚሳኤሎችን ጨምሮ የተለያዩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ታጥቋል።