የሰሜን ኮሪያ ጦር ለሩሲያ ተሰልፎ በዩክሬን እየተወጋ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ተናገሩ
በሁለቱ ሀገራት መካከል እያደገ የሚገኘው ወታደራዊ ትብብር ከፍተኛ ስጋት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል
ሩሲያ ከዩክሬን የቀረበውን ክስ ሀሰተኛ ዜና ስትል አጣጥለዋለች
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪ የሰሜን ኮርያ ጦር ለሩሲያ ወግኖ በዩክሬን እየተወጋ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በጦር መሳሪያ እና በሰው ሀይል ድጋፍ በሀገራቱ መካከል እየተጠናከረ የሚገኘው ወታደራዊ ትብብር ከፍተኛ ስጋትን ደቅኗል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ምዕራባውያን አጋሮቻቸው ጉዳዩን በትኩረት እንዲመለከቱት ጠይቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ትላንት ምሽት ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት “በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ከአጋሮቻችን ጋር ያለን ግንኙነት መሻሻል እንዳለበት ግልፅ ነው ፤ በግንባር ላይ የሚገኝው የዩክሬን ጦር ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልገዋል፤ እያወራን ያለነው ስለ ተጨማሪ የረጅም ርቀት ሚሳይሎች ድጋፍ እና ለሠራዊታችን መደረግ ስለሚገባው ተጨማሪ ቀጣይነት ያለው ወታደራዊ እገዛ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ስምምነት ከመፈጸማቸው በፊትም ሰሜን ኮሪያ ሰራሽ ሚሳይሎች እና የጦር መሳርያዎች ጥቅም ላይ ስለመዋላቸው ምልክቶች አግኝተናል ነው ያሉት፡፡
ከወራት በፊት ወደ ሰሜን ኮሪያ ያቀኑት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፒዮንግያንግ ጋር ወታዳራዊ ትብብር ስምምነት ከፈጸሙ በኋላ ደግሞ የሰሜን ኮርያ ጦር በሰፊው በዩክሬን እየተዋጋ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንት የደቡብ ኮርያ የመከላከያ ሚንስትር ኪም ዮንግ ሂዩን በፓርላማው ባደረጉት ንግግር ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ግዛቶች በተፈጸመ ጥቃት የሰሜን ኮርያ ጦር አባላት መገደላቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በቀጣይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰሜን ኮሪያ ጦር ለሩሲያ ለመዋጋት ወደ ዩክሬን ሊላክ እንደሚችል ሚንስትሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ክሪምሊን ጉዳዩን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ሁለቱ ሀገራት ስለሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ተሳትፎ ዙርያ ያወጡት መረጃ የተሳሳተ እና ከእውነት የራቀ ነው ብሏል፡፡
የክሪምሊን ቃል አቀባ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሁለቱ ሀገራ የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት አንዱ ሀገር ሲጠቃ ሌላኛው ሀገር ወታደሮችን ለመላክ እና የጦር መሳርያ ድጋፎችን ለማድረግ ቢስማሙም በዩክሬን ጦርነት ግን የሰሜን ኮሪያ ጦር እየተሳተፈ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው በደቡብ ኮርያ እና በዩክሬን ስለሰሜን ኮርያ ጦር ተሳትፎ እየተነገረ የሚገኝው ጉዳይ ሁነኛ ማረጋገጫ ከተገኝበት አሜሪካ በሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ልትጥል ትችላለች፡፡