ታይዋን የጦር መሳሪያ ቆጠራ ማድረጓን አስታውቃለች
ታይዋን የሶስት ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያዋ እንደጠፋባት ገለጸች፡፡
የቻይና የግዛት አካል አለመሆኗን የምትናገረው ታይዋን የጦር መሳሪያ ቆጠራ ማድረጓን አስታውቃለች፡፡
ከዚህ ቆጠራ በኋላም 430 ሺህ አይነት የጦር መሳሪያ ዝርዝሮች የት እንዳሉ እንዳልታወቁ ተገልጿል፡፡
በጦር መሳሪያ ኦዲት መሰረትም 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያዎች ወረቀት ላይ እንጂ በአካል የሉም ተብሏል፡፡
የታይዋን መከላከያ ተቋምም የጦር መሳሪያዎቹ የት እንዳሉ ማብራራት አልቻለም የተባለ ሲሆን የጠፉት የጦር መሳሪያዎች አይነት ግን ይፋ አልተደረገም፡፡
እንደ ራሺያ ቱዳይ ዘገባ ከሆነ በተለይም ከባህር ሀይል መርከብ ላይ የሚጠመዱ እና የሚጠመዱ የጦር መሳሪያዎች ጠፍተዋል ተብሏል፡፡
አሜሪካ እና ቻይና በታይዋን ጉዳይ መካረር ውስጥ የገቡ ሲሆን በተለይም የቀድሞ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ ታይዋንን ከጎበኙ በኋላ ግንኙነቱ ሻክሯል፡፡
ቻይና ታይዋን የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትል ሲሆን ምዕራባዊያን ሀገራት ግን ይህንን አይቀበሉም፡፡
ታይዋንን በማንኛውም መንገድ ወደ ቻይና እንደምትቀላቅል የምትገልጸው ቤጂንግ በዚህ ምክንያት ወደ ጦርነት ልትገባ እንደምትችልም አስታውቃለች፡፡
አሜሪካ ቻይና በታይዋን ላይ ጦር ልታዘምት ትችላለች በሚል የተለያዩ ድጋችን በመስጠት ላይ ትገኛለች፡፡ ከነዚህ መካከል የጦር መሳሪያ ዋነኛው ሲሆን ቤጂንግ በበኩሏ ተደጋጋሚ ታይዋንን ማዕከል ያደረገ የጦር ልምምድ ማድረጓን ቀጥላለች፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ቻይና ኢኮኖሚዋን ለጦርነት እያዘጋጀች ስለመሆኗ የተዘገበ ሲሆን በተለይም ጦርነት ቢጀመር እና ማዕቀቦች ቢፈጠሩ በሚል አማራጭ የንግድ እና ግብይት መንገዶችን መከተል፣ የነዳጅ እና ምግብ ክምችትን ማሳደግ የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡