የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ከሁለት ሳምንት በፊት ታይዋንን መጎብኘታቸው ይታወሳል
ቻይና በታይዋን አቅራቢያ ዳግም የጦርነት ልምምድ ጀመረች፡፡
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ከሁለት ሳምንት በፊት ታይዋንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ቻይና ታይዋንን በስድስት አቅጣጫ በመክበብ የጦርነት ልምምድ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ቻይና በአፈ ጉባኤዋ ጉብኝት መበሳጨቷን ገልጻ ለአንድ ሳምንት የታይዋንን የአየር ክልል በከፊል በመዝጋት ባደረገችው ልምምድ የአጭር እና የቅርብ ርቀት ሚሳኤሎችን ከመተኮስ ጀምሮ የባህር ላይ እና ሌሎች የዉጊያ ልምምድ አድርጋም ነበር፡፡
ይህ በሆነ በቀናት ውስጥ ደግሞ የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ታይዋንን መጎብኘታቸውን ተከትሎም ዳግም በታይዋን አቅራቢያ የጦር ልምምዷን ጀምራለች፡፡
የቻይና መከላከያ ባወጣው መግለጫ ጦሩ የቻይናን ሉዓላዊነት ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ገልጾ አሜሪካ በተደጋጋሚ የቻይናን ሉዐላዊነት ለመጣስ እየሞከረች መሆኑን ገልጿል፡፡
ከዚህ በፊት የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታይዋንን መጎብኘቷ እና አሁን ደግሞ የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባል የሆኑ ሰዎች ታይዋንን መጎብኘታቸው የቻይናን ሉዓላዊነት መዳፈር መሆኑንም አክሏል፡፡
በመሆኑም የቻይና ጦር የሀገሪቱ ሉዓላዊነት ሲጣስ ዝምብሎ መመልከት ስለሌለበት ለዉጊያ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና የቻይና መንግስት ልዑክ ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት በትናንትናው ዕለት ታይዋን መዲና ታይፔ የደረሰ ሲሆን ከታይዋን መሪዎች ጋር እንደሚመክር ተገልጿል፡፡
ቻይና ታይዋን የግዛቴ አንድ አካል ነች ብላ የምታምን ሲሆን አሜሪካ ደግሞ ታይዋን ሉዓላዊ ሀገር ናት የሚል አቋም በመያዝ የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ላይ ናት፡፡