የአሜሪካ ሕግ አውጭ አካላት በታይዋን ጉብኝት አድርገዋል
በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ፤ ከሰሞኑ ታይዋንን የጎበኙትን የአሜሪካ ሕግ አውጭ ባለስልጣናት አስጠነቀቀ፡፡
የአሜሪካ ህግ አውጭዎች ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ትናንትና ታይዋን የገቡ ሲሆን፤ ይህም የሁለቱን ሀገራት ፍጥጫ እንዲካረር አድርጎታል።
የህግ አውጭዎቹ ጉብኝት፤ የአሜሪካ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በታይዋን ካደረጉት ጉብኝት ቀጥሎ ታይዋንን የጎበኘ የከፍተኛ ባለስልጣናት የልኡክ ቡድን ነው።
ይህንን ጉብኝት ተከትሎም በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ የማያወላውል እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል፡፡
የፔሎሲ የታየዋን ጉብኝት ብስጭት ያልወጣላት ቤጅንግ አሁን ደግሞ ሕግ አውጭዎቹ ዳግም ወደ ታይዋን ማምራታቸው የበለጠ አስቆጥቷታል፡፡
ወደ ታይዋን ያመራው ልዑክ ቡድኑ ከታይዋን ፕሬዝደን ጻይ ኢንግ ዌን ጋር የተገናኙ ሲሆን ቤጅንግ ግን አሁንም እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች፡፡
የታይዋን ፕሬዚዳንታዊ ጽህፈት ቤት ቡድኑ ዛሬ ከፕሬዝዳንት ጻይ ኢንግ ዌንግ ጋር ተገናኝቷል፡፡
በአሜሪካ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ፤ ዋሸንግተን ከታይዋን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ማድረግ እንደሌለባት አሰሳስቧል፡፡
የአሜሪካ ሕግ አውጭዎች በታያዋን ጉብኝት ማድረጋቸው ዋሸንግተን አካባቢው እንዳይረጋጋ ፍላጎት እንዳላት ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
የአሜሪካ የአሁኑ ድርጊት ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት እንዲበላሽ የመፈለጓ ምልክት እንደሆነም ነው በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያስታወቀው፡፡
ዋሸንግተን፤ በቻይና የውስጥ ጉዳይ መግባቷ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት እንደሌለው ኤምባሲው ገልጿል፡፡ በአካባቢው ለሚነሳው የትኛውም ችግርና ውጥረት አሜሪካ ተጠያቂ እንደሆነችም ነው ቤጅንግ የገለጸችው፡፡
የአሜሪካ ኮንግረንስ አባላት ታይዋን የቻይና አካል መሆኗን ሊያሰምሩበት እንደሚገባም ቻይና አሳስባለች፡፡
በፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት የተቆጣችው ቻይና፤ በታይዋን ዙሪያ ወደራዊ ልምምድ አድርጋለች፤ በፔሎሲም ላይ ማእቀብ ጥላለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቻይና ከአሜሪካ ጋር የነበራትን ወታደራዊ ትብብር ማቋረጧን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡