በጃፓን የቻይና አምባሳደር፤ ጃፓን በቻይና የውስጥ ጉዳይ መግባት አልነበረባም ብለዋል
ጃፓን፤ በቻይና የውስጥ ጉዳይ የመግባት መብት እንደሌላት በቶኪዮ የሚገኙት የሀገሪቱ አምባሳደር ተናግረዋል፡፡
በጃፖን የቻይና አምባሳደር ኮንግ ዣንዩ፤ ጃፓን ከአሜሪካ ወገን ሆና የቻይናን ጥቅም መንካት እንዳልነበረባት ተናግረዋል፡፡
ዲፕሎማቱ ይህንን ያሉት ከጃፓናውያን ጋር ባደረጉት ውይይት መሆኑን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡ ቻይና፤ በታይዋን ጉዳይ ግልጽ አቋም እንዳላት የገለጹት አምባሰደሩ፤ ጃፓን ግን ከአሜሪካ ጎን መቆም የለባትም ብለዋል፡፡
ቻይና፣ በአሜሪካ ላይ የምትወስዳቸው እርምጃዎች ጃፓንን እንደማይመለከቱም ነው ዲፕሎማቱ ያነሱት። አምባሳደሩ፤ ጃፓን በታይዋን ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር "መደነስ የለባትም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጃፓን፤ አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ ላይ ያራመደችውን አቋም መደገፏ የቤጅንግንና የቶኪዮን ወዳጅነት እንደሚያሻክርም ነው ቻይና የገለጸችው።
ጃፓን፤ ታይዋንን በህገ ወጥ መንገድ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ስትቆጣጠር መቆየቷን የገለፁት የቻይናው አምባሳደር ፤ ቶኪዩ ያለፈውን ጥፋት መድገም የለባትም ብለዋል።
በዚህ ዓመት የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት 50 ኛ ዓመት መሙላቱን የተናገሩት ዲፕሎማቱ ፤ ጃፓንም ወዳጅነትን ማጠናከር ላይ ማተኮር እንደሚገባት አሳስበዋል።
ቻይና የታይዋን ጉዳይ የማትደራደርበት መሆኑን ገልጻለች። ጃፓንም ይህንኑ የማክበር ግደታ እንዳለባት ቤጅንግ አሳስባለች። ጃፓን ደግሞ በሩቅ ምስራቅ የአሜሪካ ዋነኛ አጋር ናት።
የአሜሪካ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎስ ቻይና የግዛቷ አንድ አካል አድርጋ የምታያትን ታይዋንን መጎብኘታቸውን ተከትሎ አሜሪካ እና ቻይና የከረረ መፋጠጥ ውስጥ ገብተዋል፤ በቀጠናውም ውጥረቱ አይሏል፡፡