የቻይና ድርጊት “ታይዋን ነጻነቷን ከማወጅ እንድትቆጠብ የሚያስጠነቅቅ” መሆኑ ተንታኞች ይገልጻሉ
ቻይና 30 የጦር አውሮፕላኖችን ወደ ታይዋን የአየር መከላከያ ቀጠና ላከች፡፡
የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር በቀጠናው የቻይና ድርጊት 22 ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖች፣ የጸረ-ሰርጓጅ መርከብና ቅድመ ማስጠንቀቂያ አውሮፕላኖች መታየታቸውን ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ የጦር አውሮፕላኖቹ "ፓራታስ" ተብሎ በሚታወቀውና የአየር መከላከያ ስፍራ በሆነው የታይዋን ሰሜን ምስራቅ ክፍል አካባቢ መብረራቸውን አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ አውሮፕላኖቹ የታይዋን አየር ክልል ጥሰው እንዳልገቡ ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡
ሃገራት የአየር ቀጣናን እንደ ሉዓላዊ ይዞታ ይመለከታሉ፡፡ በተደራጁ የቅኝት መንገዶች የሚጠበቁ የራሳቸው የአየር መከላከያ ቀጣናዎችም አሏቸው፡፡ በዚህም ያለ ፈቃድ የአየር ክልሉን ጥሶ የሚገባም ሆነ የሚያልፍ አይኖርም፡፡
የአሁኑ የቻይና ድርጊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቻይና ታይዋንን ከመውረር እንድትቆጠብ የሚል ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ ከሰጡ ከጥቂት ቀናት በኋላ በትናንትናው እለት የሆነ ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ወደ ታይዋን በማቅናት አሜሪካ እና ታይዋን በጸጥታ ጉዳዮች በጋራ በሚሰሩባቸው የትብብር ማእቀፎች ዙርያ ከመከሩ በኋላ የሆነ እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
የጦር አውሮፕላኖች ወደ ታይዋን የአየር ክልል ዘልቀው መግባታቸው ታይዋንንና የምዕራቡ ዓለም አጋሮቿን ቢያስቆጣም፤ ቻይና ግን ልምምድ ለማድረግ መሆኑ በመግለጽ ላይ ናት፡፡
ቻይና የጦር አውሮፕላኖቿ በወርሃ ጥር በተመሳሳይ መልኩ ወደ ታይዋን የአየር ክልል እንዲገቡ አድርጋ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ታይዋንን እንደ አንድ ለመገንጠል ጫፍ ላይ እንዳለች የግዛት አካሏ አድርጋ የምትመለከተው ቻይና፤ አስፈላጊ ከሆነ በጉልበትም ልትመልሳት እንደምትችል በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ታይዋን የቻይና አውሮፕላኖች የአየር መከላከያ ክልሏ ዘልቀው እየገቡ መሆናቸው መናገር ከጀመረች አንድ አመት ተቆጥሯል፡፡ ሆኖም ይህ የቻይና ድርጊት ታይዋን ነጻነቷን ከማወጅ እንድትቆጠብ የሚያስጠነቅቅ መሆኑ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡
ቤጂንግ ከዚህ በፊት በሰጠችው መግለጫ “ሉዓላዊነቴን ለማስጠበቅ የማደርገው ልምምድ ነው” ማለቷ ይታወሳል፡፡
ባይደን ባሳለፍነው ሳምንት በእስያ ባደረጉት ጉብኝት የሀገራት የአየር ክልሎችን ስለመጣስ ጉዳይ አንስተው መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ቻይና "ለታይዋን በጣም ተጠግታ የምታደርገው በረራ አደጋ ሊያስከትል ይችላል" ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል አስተያየትም ነበር የሰነዘሩት፡፡
ቻይና በታይዋን ላይ ወረራ ከፈጸመች፤ አሜሪካ ወታደራዊ አጸፋ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንቱ መናራቸውም የሚታወስ ነው፡፡