ቻይና ከአሜሪካ ወደ ሀገሯ የሚገቡ የኃይል ምርቶች ላይ የ15 በመቶ ታሪፍ እጥላለሁ ብላለች
በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በምርቶቿ ላይ ታሪፍ የተጣለባት ቻይና የአጸፋ እርምጃ መውሰድ መጀመሯን አስታውቃለች።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በቻይና ምርቶች ላይ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የ10 በመቶ ታሪፍ መጣሉን አስታቋል።
ይህንን ተከትሎም ቻይና ከአሜሪካ ወደ ሀገሯ የሚገቡ የኃይል ምርተች ላይ የ15 በመቶ ታሪፍ እንደምትጥል አስታውቃለች።
በተጨማሪም ቻይና በአሜሪካው ጎግል ኩባንያ ላይ በዛሬው እለት ተዓማኒነት ምርመራ እንደምትጀምርም አስታውቃለች።
የቻይና የንግድ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ በአሜሪካ የክሰል ድንጋይ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ላይ የ15 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣል አስታውቋል።
በተጨማሪም በአሜሪካ ድፍድፍ ነዳጅ፣ የግብርና መሳሪያዎች እና ግዙፍ ተሸከርካሪዎች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ መጣሉን ሚኒስቴሩ አስውቋል።
የሚኒስቴሩ መግለጫው “የአሜሪካ የአንድ ወገን ታሪፍ ጭማሪ የዓለም ንግድ ድርጅትን ህግጋት በእጅጉ የጣሰ ነው” ብሏል።
“እንዲህ አይነት ውሳኔዎች ጥቅም የላቸውም” ያለው ሚኒስቴሩ፤ “በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለውን መደበኛ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር ይጎዳል" ሲልም አሳስቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በካናዳ፣ ሜክሲኮ እና በቻይና ላይ ታሪፍ የሚጥል ትእዛዝ መፈራረማቸው ይታወሳል።
በፕሬዝዳንት ትራምፕ ትእዛዝ መሰረትም በካናዳና ሜክሲኮ የ25 በመቶ፤ በቻይና ላይ ደግመፐ የ10 በመቶ ታሪፍ የሚጣል ተብሎ ነበር።
ትራምፕ በሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ያሳለፉትን ውሳኔ ለአንድ ወር እንዲዘገይ ማድረጋቸውን በዛሬው እለት አስታውቀዋል።
ትራምፕ ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እና ከሜክሲኮ አቻቸው ክላውዲያ ሺሜንባም ጋር በስልክ ከመከሩ በኋላ ነው ታፉን ለአንድ ወር ማራዘማቸውን ያስታወቁት።