ትራምፕ በሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ ሊጣል የነበረውን የ25 በመቶ ታሪፍ ለአንድ ወር አራዘሙ
የካናዳ እና ሜክሲኮ መሪዎች የህገወጥ ስደተኞችን ፍሰት ለመቆጣጠርና የአደንዛዥ እጽ ዝውውርን ለመግታት ከትራምፕ ጋር ስምምነት ደርሰዋል
በቻይና ላይ የሚጠላው የ10 በመቶ ታሪፍ ግን ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ያሳለፉትን ውሳኔ ለአንድ ወር እንዲዘገይ ማድረጋቸውን አስታወቁ።
ትራምፕ ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እና ከሜክሲኮ አቻቸው ክላውዲያ ሺሜንባም ጋር በስልክ መክረዋል።
በዚህም ሁለቱ ሀገራት የህገወጥ ስደተኞችን ፍሰት ለመቆጣጠር የድንበር ቁጥጥራቸውን ለማጥበቅና የአደንዛዥ እጽ ዝውውርን ለመግታት ከትራምፕ ጋር ስምምነት መድረሳቸውን ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ካናዳ "ፌንታይል" የተሰኘውን አደንዛዥ እጽ ዝውውር ለመግታት ከአሜሪካ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ተጨማሪ የሰው ሃይል እንደምታሰማራ ገልጸዋል።
ሜክሲኮም በሰሜናዊ የሀገሪቱ ድንበር 10 ሺህ የብሄራዊ ዘብ አባላትን በማሰማራት የህገወጥ ስደተኞች እና አደንዛዥ እጽ ዝውውርን ለመቀነስ ስምምነት ላይ መድረሷን ፕሬዝዳንት ክላውዲያ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ስምምነቱ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረግ የነበረውን ታሪፍ ለአንድ ወር እንዲራዘም ማድረጉንም ሬውተርስ ዘግቧል።
በቀጣይ 30 ቀናት ከካናዳ እና ሜክሲኮ ጋር ተከታታይ ድርድሮች እንደሚካሄዱ ያስታወቁት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፥ በቻይና ምርቶች ላይ የተጣለው የ10 በመቶ ታሪፍ ግን ከዛሬ ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።
"ቻይና ወደ ሀገራችን ፌንታኒል መላክ ማቆም አለባት፤ ይህን ካላደረገች ግን የምንጥለው ታሪፍ ከዚህም ከፍ ሊል ይችላል" በሚል ያስጠነቀቁት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ ቀናት ከቤጂንግ ጋር ምክክር እንደሚደረግ መናገራቸውን ፍራንስ 24 አስነብቧል።
አወዛጋቢው ፕሬዝዳንት በሜክሲኮ እና ካናዳ ምርቶች ላይ የሚጣለው የ25 በመቶ ታሪፍ ለአንድ ወር ይራዘማል ባሉበት እለት የአውሮፓ ህብረት ቀጣዩ የታሪፍ ጭማሪው ኢላማ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
27ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ከአሜሪካ ተሽከርካሪዎችንም ሆነ የግብርና ምርቶችን እንደማይገዙና አሜሪካ ግን የሀገራቱ ሸቀጦች መራገፊያ መሆኗን በመጥቀስም ታሪፍ እንጥላለን ብለዋል።
በብራሰልስ መደበኛ ያልሆነ ጉባኤ ያደረጉት የህብረቱ መሪዎች ግን ትራምፕ ለሚጥሉት ታሪፍ ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት እንዲደረግ አሳስበዋል።
የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት ወደ አሜሪካ በሚገቡት ሸቀጦች ላይ የሚጣለው ታሪፍ በዜጎች ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር እንደሚያደርግ ባይክዱም ህገወጥ የሰዎች እና የአደንዛዥ እጽ ዝውውርን ለመግታት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
የታሪፍ ጭማሪው አሜሪካ ከውጭ ከምታስገባቸው ምርቶች ግማሽ የሚጠጋውን የሚይዝ እንደመሆኑ ክፍተቱን ለመድፈን የአሜሪካውያን አምራቾች አቅም በእጥፍ ማደግ ይኖርበታል። ይህም አመታትን ሊወስድ ይችላል የሚሉ ተንታኞች በአጭር ጊዜ የሚሳካ እንዳልሆነ ያነሳሉ።