ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለስልጣናት ሞስኮ፤ የቤጅንግን ድጋፍ ጠይቃለች ብለው ነበር
ከትናንት ጀምሮ ሩሲያ፤ ቻይናን ወታደራዊ ድጋፍ እንድታደርግላት መጠየቋን የሚገልጽ ዜና ሲሰራጭ ነበር፡፡
ይሁንና እነዚህ የዜና ማሰራጫ ጣቢያዎች ሞስኮ አሁን እያካሄደችው ላለው ወታደራዊ ተልዕኮ ከቤጂንግ ድጋፍ ጠይቃለች በሚል ቢዘግቡም ቻይና ግን ጉዳዩ ትክክል እንዳልሆነ አስታውቃለች፡፡
ሩሲያ፤ ቻይና ወታደራዊ ድጋፍ እንዲታደርግላት መጠየቋን ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለስልጣናት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግረው እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ለጉዳዩ ሽፋን ከሰጡት መካከል አንዱ የሆነው ፋይናንሻል ታይምስ ሲሆን ሩሲያ፤ ቻይና የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችንና በዝርዝር ያልተገለጹ ወታደራዊ ድጋፎችን እንድታደርግላት ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር፡፡
ከዚህ ባለፈም ኒውዮርክ ታይምስ፣ ሲኤንኤን፣ እንዲሁም ሌሎች ሚዲያዎች ሩሲያ፤ ቻይና የድሮን ድጋፍ እንድታደርግላት ጠይቃለች በሚል ዘገባዎችን ሲያሰራጩ ነበር፡፡ ቻይና ግን መገናኛ ብዙኃኑ እየዘገቡት ባለው ጉዳይ ላይ ምንም የተሰማ ነገር እንደሌለ አስታውቃለች፡፡
በአሜሪካ ያለው የቻይና ኤምባሲ ሞስኮ እና ቤጂንግን በተመለከተ የተሰራጨው ዜና ሙሉ በሙሉ ሃሰት መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሊዩ ፔንግዩ፤ ጉዳዩ ሀሰት መሆኑን ገልጸው፤ ቻይና አሁን ያለው የዩክሬንና የሩሲያ ውጥረት እንዲቀንስ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ሚዲያዎቹ ሩሲያ፤ ቻይና ወታደራዊ ድጋፍ እንድታደርግላት ጠየቀች የሚለውን ጉዳይ ቤጂንግ እንደማታውቅ ነው ኤምባሲው የገለጸው፡፡
አሁን ላይ የቻይና ዋነኛ ዓላማ ውጥረትን መቀነስና የተፈጠሩ ችግሮችን መፍታት ነው ብለዋል፡፡