የቻይና አረብ ጉባኤ ለሁለትዮሽ ግንኙነት ጠቀሜታ እንዳለው ቤጂንግ ተናግራለች።
ቻይና ከኢራን ጋር ያላትን ወዳጅነት ቸል እንደማትለው አስታወቀች፡፡
የቻይና እና የባህረ ሰላጤው የትብብር ም/ቤት ጉባኤ ለሁለቱ ወገኖች ግንኙነት ትልቅ ትርጉም እንዳለው የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ተናግሯል።
የሁለቱም ወገኖች መሪዎች በቻይና-የገልፍ ትብብር ም/ቤት ፖለቲካዊ መተማመኛነት እና በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር በማሳደግ ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን አስታውቀዋል።
በቻይና እና በም/ቤቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት የሁለትዮሽ ተግባራዊ ትብብርን በተለያዩ ዘርፎች ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል።
ቻይና ከም/ቤቱ ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት ከኢራን ጋር ያላትን ወዳጅነት ቸል እንደማትል የጠቀሱት ቃል አቀባዩ ቻይና እና ኢራን ባህላዊ ወዳጅነት እንዳላቸው እና በጋራ ለመስራት እንዲሁም አጠቃላይ ስልታዊ አጋርነትን ለማሳደግ ወስነዋል ብለዋል።
"ቻይና ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት እና ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ አዲስ መሻሻል ለማድረግ ዝግጁ ነች" ሲሉ ዋንግ ተናግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ አጠቃላይ የትብብር እቅድ የተፈራረሙ ሲሆን፤ ቻይና ከኢራን ጋር ለተግባራዊ ትብብር፣ ጤናማ እና ቀጣይነት ያለው እድገት እንደምትሰራም ተናግረዋል።
ዋንግ እንዳሉት የባህረ ሰላጤው ሀገራት እና ኢራን ሁሉም የቻይና ወዳጆች ሲሆኑ፤ የቻይናና የም/ቤቱ ግንኙነትም ሆነ የኢራን ግንኙነት በሦስተኛ ወገን ላይ ያነጣጠረ አይደለም ማለታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ቻይና የባህረ ሰላጤው ሀገራትን ከኢራን ጋር ግንኙነታቸውን ማሳደግ እንደምትደግፍ ተናግራለች።
ከኢራን ጋር ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ትብብር ለማድረግ እና በፋርስ ባህረ ሰላጤ ያለውን ልማት እና መረጋጋት በጋራ ለማሳደግ ቤጂንግ ገንቢ ሚና መጫወቷን ትቀጥላለች ተብሏል።