ሁለቱ ሀገራት የተፈራረሟቸው ስምምነቶች 30 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው እንደሆነ ተገልጿል
ቻይና እና ሳዑዲ አረቢያ በ34 የኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
የዓለማችን ሁተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገር ቻይና ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስምምነት ተፈራርማለች።
ስምምነቱን ሳውዲ አረቢያን እየጎበኙ ያሉት የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጅንፒንግ እና የሳዑዲ አረቢያ አልጋወራሽ ልዑል መሀመድ ቢን ሳልማን መፈራረማቸውን የሳዑዲ አረቢያ ዜና ወኪል ዘግቧል።
ሁለቱ ሀገራት በ34 የኢንቨስትምነት መስኮች በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲሆን በሎጅስቲክስ፣ በታዳሽ ሀይል ልማት፣ በህክምና፣ በትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ፣ በቴክኖሎጂ እና ግንባታ ዘርፎች ሁለቱ ሀገራት ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
የሳዑዲ አረቢያ ኢንቨስትመንት ሚኒስትር ካሊድ ቢን አብዱላዚዝ ስለ ስምምነቱ ለብዙሃን መገናኛዎች እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት ስምምነት ትብብራቸውን ከማጠናከሩ ባለፈ ዘላቂ የንግድ እና ኢንቨስትምንት እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም አዲስ የተፈረመው ስምምነት ሳውዲ አረቢያ ለቀረጸችው ራዕይ 2030 ተፈጻሚነት የሚያግዝ ሲሆን በተለይም ሳዑዲ በታዳሽ ሀይል ልማት፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝም እና ሌሎች ስራዎችን እንደሚያቀላጥፍ ተናግረዋል።
የቻይና እና ሳውዲ አረቢያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መጠን 80 ቢሊዮን ዶላር ያለፈ ሲሆን በተያዘው ዓመት ውስጥ ደግሞ የ270 ሚሊዮን ዶላር ንግድ ተለዋውጠዋል ተብሏል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጅፒንግ ነገ በሚጀመረው የቻይና-አረብ ጉባኤ ላይ እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን የመካከለኛው መስራቅ ሀገራት በዚህ ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
የሳውዲ ዜና አገልግሎት ከቀናት በፊት ባወጣው ዘገባ ቻይና እና ሳዑዲ አረቢያ 30 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ዋጋ ያላቸው የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስምምነት እንደሚፈራሙ መግለጹ ይታወሳል።