ቻይና ኢትዮጵያ ከ1 ሺህ በላይ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገሯ እንድታስገባ ፈቀደች
“የቻይና ከቀረጥ ነጻ የገበያ እድል በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት ግዴታ አይጥልም” የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር
ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንድታስገባ ከተፈቀዱ ምርቶች መካከል ዋነኞቹ የትኞቹ ናቸው…?
የቻይና መንግስት ኢትዮጵያ ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና ገበያ እንድታስገባ መፍቀዱ ተገለፀ።
በዚህም ቻይና ኢትዮጵያ 1 ሺህ 644 ምርቶች ከቀረጥና ኮታ ነጻ ማስገባት እንደምትችል መፍቀዷን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና ገበያ እንድታስገባ ከተፈቀዱ ምርቶች መካልም እንደ በግ፣ ፍየል እና ገመል ያሉ የቁም እንስሳት ስጋ እና የስጋ ውጤቶች እንዲሁም የተፈጥሮ ዉሃ ይገኙበታል።
- ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ውስጥ ተካታለች
- ቻይና “የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ጠንካራና የማይሰበር ነው” ማለቷን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ
በተጨማሪም እንደ ባቄላ እና ቦሎቄ ያሉትን ጨምሮ ጥራጥሬዎች፣ ሰሊጥ፣ ስንዴ (የስንዴ ዱቄት እንዲሁም ዱረም ስንዴን ጨምሮ)፣ በቆሎ እና አጃም ከቀረጥ ነጻ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
ስኳር ድንች፣ አቮካዶ፣ ብረቱካን ሀብሃብ፣ የወይን ፍሬ እንዲሁም ሌሎች ፍራፍሬዎች ከቀረጥ ነጻ ፍቃድ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በእጅ የተሰሩ አልባሳት እንዲሁም ከእንጨት እና ከቀርከሃ የተሰሩ የቤት እና የቢሮ መገልገያዎች ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንድታስገባ መፈቀዱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው ዝርዝር አመላክቷል።
“ቻይና ለኢትዮጵያ የፈቀደችው ከቀረጥ ነጻ የገበያ እድል በቻይና በኩል የተሰጠ ነው” ያለው ሚኒስቴሩ፤ “በኢትዮጵያ ላይ ምንመ አይነት ግዴታን አይጥልም” ሲልም አስታውቋል።