ቻይና አዲስ አምባሳደር የላከችው አሜሪካም ተመሳሳይ ሚና ያለው ዲፕሎማት ከመደበች ከዘጠኝ ወራት በኋላ ነው
ቻይና፤ በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ የመደበቻቸውን ዲፕሎማት ሥም ይፋ ማድረጓን አስታወቀች፡፡
አምባሳደር ሹ ቢንግ በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ሆነው መሾማቸውን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡ በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች መምሪያ ዋና ዳይሬክተር ው ፔንግ፤ ከዚህ በኋላ በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ወካይ ዲፕሎማት ሆነው የሚሰሩት አምባሳደር ሹ ቢንግ ናቸው መሆናቸውን በይፈዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፤በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማትን እንዲጎለብት እንደምትሰራም አስታውቋል፡፡ ለማበረታታት እንደምታሰራም ተገልጿል፡፡ ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ የሾመችው አሜሪካ በቀጠናው ልዩ መልዕክተኛ ከሾመች ከዘጠኝ ወራት በኋላ ነው፡፡ ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እንደምትሾም የተገለጸው የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በኬንያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነበር፡፡
ቻይና የምትሾመው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በቀጠናው ያሉ ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን የፀጥታ እና ደህንነት ስጋቶችን ለመቀልበስ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ እንደሆነም ቻይና ገልጻለች፡፡
የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሁሉም ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ላይ ያተኮረ ጉባዔ እንዲያደርጉ ሃሳብ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ከዘጠኝ ወራት በፊት የአፍሪካ ቀንድን ሁኔታ “ለመከታተል” በሚል በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ ቀድሞ ያልነበረ አዲስ መዋቅር በመማምጣት ልዩ መልዕክተኛ መመደቧ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት ዋሸንግተን ጄፍሪ ፌልትማንን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ ሾማ የነበረ ቢሆንም አሁን ፌልትማን በሳተር ፊልድ ተተክተዋል፡፡