ኢትዮጵያ በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ምርመራ ወቅት ጫና ይደርስባት እንደነበር ተገለጸ
የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የመጨረሻ የምርመራ ሪፖርት ይፋ ሆኗል
2011 ዓ.ም በደረሰው አደጋ ስምንት የበረራ አስተናጋጆችን ጨምሮ 157 ተሳፋሪዎች ህይወት ማለፉም አይዘነጋም
ኢትዮጵያ በቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላን ምርመራ ወቅት ጫና ይደርስባት እንደነበር ተገለጸ።
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው እና የበረራ ቁጥሩ ኢቲ 302 ማክስ 737- 8 አውሮፕላን መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ኬንያ ሙዲና ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ ቢሾፍቱ አቅራቢያ መከስከሱ ይታወሳል።
በአደጋውም ስምንት የበረራ አስተናጋጆችን ጨምሮ 157 ተሳፋሪዎች ህይወት ማለፉም አይዘነጋም።
የዚህ አውሮፕላን አደጋ ምርመራ ሪፖርት አደጋው በተከሰተ ከአንድ ወር በኋላ ይፋ የተደረገ ሲሆን ከዚህ ሪፖርት ጋር ተመሳሳይነት ያለው የመጨረሻ ምርመራ ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚንስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ሪፖርቱ መዘግየቱን ጠቅሶ የኮሮና ቫይረስ መከሰት ለሪፖርቱ መዘግየት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተደረገው ምርመራም የበረራ ባለሙያዎች በረራ ማድረግ የሚያስችላቸው ብቃትና ፈቃድ እንዳለቸው መረጋገጡን ፣ አውሮፕላኑ መብረር የሚያስችል የምስክር ወረቀት ያለው መሆኑ እና አውሮፕላኑ ለበረራ ሲነሳ ትክክለኛ ክበደት መሸከም በሚያስችለው ሁኔታ ላይ እንደነበር መረጋገጡን ተናግረዋል።
ለአውሮፕላኑ መከስከስ ዋነኛ ምክንያትም MCAS የተሰኘው ሶፍትዌር በትክክል አለመስራት መሆኑን ወ/ሮ ዳግማዊት አስታውቀዋል።
በምርመራው ሪፖርቱ መሰረትም የማክስ 737-8 ማክስ አውሮፕላን ኤምካስ የተሰኘው የአውሮፕላኑ ፍጥነት እና አቅጣጫ መቆጣጠሪያ በተደጋጋሚ ወደ ታች ማጎንበሱ የአደጋው ምክንያት እንደሆኑ ተገልጿል።
ይህ የተከሰከሰው አውሮፕላን የበረራ ፈቃድ፣ አብራሪ እና የበረራ መስመሩ የታወቀ እና የተፈቀደ እንደነበር ሚንስትሯ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል።
በአደጋው ምርመራ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ ከባድ ጫናዎች እንደነበሩ የተናገሩት ሚንስትሯ ጫናዉን ተቋቁመን ሪፖርቱን አጠናቀናል ብለዋል።
ይሁንና ሚንስትሯ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ያደረሱትን አካላት እና የጫናውን ምንነት ከመናገር ተቆጥበዋል።
በዚህ የምርመራ ሪፖርት መሰረት የአውሮፕላኑ አምራች ኩባንያ ወይም ቦይንግ ማስተካከያ አድርጎ አውሮፕላኑን ዳግም ወደ በረራ መልሷል ተብሏል።
በአደጋው ምርመራ ወቅት ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ እና አሜሪካ ድጋፍ ማግኘቷንም ሚንስትሯ ገልጸዋል።