የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ይዞት የሚመጣው እድል ምንድን ነው?
የቱሪዝም ሚኒሰቴር የትግራይ ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴን ወደ ነበረበት ለመመለስ ዝግጁ መሆኑ አስታውቋል
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በቱሪዝም ዘርፍ መሰረታዊ ምሶሶዋች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ነበር ተብሏል
በየትኛው የዓለም ክፍል ወረርሺኝ፣ ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ጦርነት በሚኖርበት ወቅት ሰው ተኮር የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ እንደሚጎዳ እሙን ነው።
ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በኩል በጦርነት ውስጥ ለቆየችው ኢትዮጵያ የነበረው የቱሩዝም እንቅስቃሴ ሁኔታም በመሳሳይ ይህንኑ የሚሳይ ነው።
በኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም መዳረሻና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በኮቪድ እና በጦርነት ተደራራቢ ችግሮች የተፈተነው የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴው ተገድቦ ቆይቷል ብለዋል።
“ጦርነቱ የዘርፉ መሰረታዊ ምሶሶዎች በሆኑ መስህቦች፣ ሙዚየምች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ኤርፖርቶች፣ ሬስቶራንቶች ላይ ውድመት እና ዝርፊያ አስከትሏል” ሲሉም አቶ ስለሺ ተናግረዋል።
- ህወሓት ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በሚገኙ የቱሪዝም ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን መንግስት አስታወቀ
- ከ3 ለሚልቁ ወራት በህወሓት ቁጥጥር ስር የነበሩት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
እንደ ቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክ ፣ ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ አክሱም ኤርፖርት፣ ላሊበላ ኤርፖርት፣ የነጋሽ (አልነጃሺ) መስጊድ እና ቅዱስ ላሊበላ ቤተክርስትያን የመሳሰሉ መስህቦች ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ጉዳት እንደደረሳበወችና ለአደጋ ተጋላጭ እንደነበሩም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የነበረው ሁኔታ ጎብኚዎች ደህንነት ተሰምቷቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ከማድረጉ በዘለለ ቀደም ሲል ይገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረቱ፣ የስራ እድሎች እንዲዘጉ ማድረጉ እንዲሁም የሀገሪቱን ገጽታ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱ ለቱሪዝም ሴክተሩ ይዞት የሚመጣው እድል ምንድን ነው?
ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ በቅርቡ በመንግስት እና ህወሐት መካከል የሰላም ስምምነቱ ተፈርሞ ወደ ትግበራ መገባቱ የሚታወቅ ነው።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ከሆነ፤ ስምምነቱ ተዳክሞ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃና ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።
“ሰላም የቱረዝም ፓስፖርት ነው” የሚሉት አቶ ስለሺ “ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትንሳኤ ወቅት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።የቱሪዝም እንቅስቀሴን ወደ ነበረበት ለመመለስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎችም ጭምር ሁኔታዎች እያመቻቸን ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አሁን ላይ ከቪዛ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የማመቻቸት ፣ ወደ ተለያዩ ሀገራት በመሄድ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብትን የማስተዋወቅ፣ ጎብኚዎች ከመጡ በኋላ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የማድረግ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ጥገና ተደርጎላቸው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የማስቻል፣ ሆቴሎች ዝግጁ የማድረግ እና በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ስልጠና የመስጠት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።
በትግራይ ክልል ባሉ መስህቦች ምን ሊሰራ ታስቧል..?
በትግራይ ክልል የሚገኘው ቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክ እና ነጋሽ ( አልነጃሺ) መስጊድ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው መስህቦች መሆናቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲዘግብ መቆየቱ አይዘነጋም።
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ፤ የቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርክ የነበሩት ተሸከርካሪዎችና የቢሮ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውና አል-ነጃሺ መስጂድ ጣራ ላይ ጉዳት መድረሱን ለአል ዐይን አረጋግጠዋል።
የደረሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ፓርኩ የተወሰነ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችለውን የተሸከርካሪወችና አንዳንድ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉ ያነሱት ሚኒሰትር ዴኤታው፤ በቀጣይ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር አስፈላጊው ጥናት ተደርጎ ወደ ጥገና እና የማስተካከል ስራ ይገባል ብለዋል።
በአማራ እና አፋር ክልል ተመሳሳይ ጥናት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት አቶ ስለሺ፤ “በትግራይ ክልል በሚገኙ እንደ ገርዓልታ ተራራ እና ደብረ ዳሞ በመሳሰሉ ሁሉም መስህቦች ላይ ተመሳሳይ ጥናት በማድረግ የትግራይ ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ በእኛ በኩል ዝግጁ ነን” ሲሉም ተናግረዋል።
ያም ሆኖ የቱሪዝም ዘርፍን ድጋሚ ለማነቃቃት በሚደረገው ጥረት ሁሉን ቀላል እንደማይሆንና ሁሉን አቀፍ ትብብር የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑም አስታውቀዋል።