ፖሊስ ፊት መልክ መለያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አባት እና ልጅን ከ22 ዓመታት በኋላ ማገናኘት ችሏል
ቻይናዊው ከ22 ዓመት በፊት የታገተበትን ልጁን አገኘ፡፡
ነገሩ የተፈጠረው ከ22 ዓመት በፊት በሀገረ ቻይና ነው፡፡ ሊ ዊዜ የተሰኘው ሰው በሚኖርበት በሁናን ግዛት ዩያንግ ከተማ የ4 ዓመት ወንድ ልጁን ጎረቤቱ እንድትጠብቅለት በሚል በስጠት ወደ ስራ ያመራል፡
ይህች ልጅን ስትጠብቅ የነበረች ጎረቤቱ ትኩረቷ በሌላ ነገር ላይ መሆኑን ያስተዋለ አንድ ግለሰብም ዩቺዋን የተሰኘውን የአራት ዓመት ህጻን ይዞ ይሰወራል፡፡
ከስራ ሲመለስ ልጁ ታግቶ እንደተወሰደበት የተረዳው አባትም ፍለጋውን ሳያቋርጥ በመላው ቻይና ሲንከራተት እንደቆየ ተገልጿል፡፡
የልጁን ፎቶ በመያዝ በየጎዳናው ሲፈልግ የቆየው ሊ በየሚዲያው እና አደባባዮች እየሄደ ቢፈልግም ልጁን አየሁ ያለ ሰው ይጠፋል፡፡
70 በመቶ ጊዜውን ልጁን በመፈለግ ሲያሳልፍ የቆየው ይህ አባት ለፖሊሶች ቢያመለክትም መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም ነበር፡፡
በመጨረሻም የቻይና ፖሊስ የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ለማፈላለግ እና ተመሳሳይ ፊት ያላቸውን ሰዎች መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ማዋሉን ተከትሎ ከ22 ዓመት በፊት የታገተው ልጅ ሊገኝ ችሏል፡፡
ሊ እና የታገተው ልጅ ዩቹዋን ሁለት ጊዜ በተደረገላቸው የዘረ መል ምርመራ አባት እና ልጅ መሆናቸው መረጋገጡን ቻይና ፕረስ ዘግቧል፡፡
ሲታገት የአራት ዓመት ህጻን የነበረው ዩቹዋን አሁን ላይ የ26 ዓመት ጎረምሳ ሆኖ በቻይናዋ ሸንዘን በመኖር ላይ ነበር ተብሏል፡፡
ይሁንና ከ22 ዓመት በፊት እገታውን የፈጸመው ግለሰብ ማንነት እስካሁን ይፋ እንዳልሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡