አዲሱ የቻይና ቴክኖሎጂ በሰከንድ እስከ 18 ኪሎ ሜትር ርቀትውስጥ የሚገኝ 20 ኢላማዎችን መለየት ይችላል
ቻይና የጠላት ድሮኖችን ከሩቁ መለየት እና ማውደም የሚችል አዲስ የፀረ ድሮን ቴክኖሎጂ ከሰሞኑ ይፋ አድርጋለች።
የ2022 የቻይና የአየር ትርኢት (ቻይና ኤር ሾው) በደቡባዊ የሀገሪቱ ከተማ ዡሃይ መካሄድ ላይ ሲሆን፤ የተለያዩ አዳዲስ የጦር ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች።
ቻይና በዚህ የአየር ትርኢት ላይ ካቀረበቻው አዳዲስ የጦር ቴክኖሎጂዎች ውስጥም የድሮን መግደያ የተባለው የፀረ ድሮን መሳሪያ እንደሚገኝበት ተነግሯል።
ቻይና ግሎባል ታይም እንደዘገበው ከሆነ፤ አዲሱ የፀረ ድሮን ስርዓት በጣም በአነስተኛ እና ጥቃቅን ሚሳኤሎች፣ የረቀቁ ሴንሰሮችን እና ራዳር በማካተት የተሰራ ነው።
በቻይና ኤሮስፔስ ሳይንስና ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የተሰራው አዲሱ ቴክኖሎጂ በአንድ ሰከንድ ውስጥ ከ500 ሜትር እስከ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኙ 20 የጠላት ኢላማዎችን መለየት እና ማጥቃት የሚችል ነው።
ከድሮኖች በተጨማሪ “DK-1” አዲሱ የቻይና ቴከኖሎጂ መሬት ላይ የሚጓዙ ተሽከርካሪ ኢላማዎችን ማወቅ እንደሚችልም ነው የተገለፀው።
በዚህም “ZK-K20” የተሰኘ በጣም ጥቃቅን የፀረ ድሮን ሚሳዔሎችን የሚተኩስ ሲሆን፤ ሚሳዔሉ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የጠላትን ድሮን በአየር ላይ መትቶ መጣል የሚችል ነው።
በቻይና ደቡባዊ ግዛት ዡሃይ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ቻይና ኤር ሾው ላይ የተለያዩ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች እና አውሮፕላኖች መቅረባቸው ተነግሯል።
ከእነዚህም ውስጥ የቻይና ጦር የታጠቀው “J-20” ስውር ተዋጊ ጄቶች ዙሃይ ሰማይ ላይ መታየታቸው የታዳሚዎችን ቀልብ መሳብ ችለዋል።
በሰዓት እስከ 2 ሺህ 100 ኪሎ ሜትር ድረስ መብረር ይችላል የተባለለት “J-20” ተዋጊ ጄት፤ 19 ሺህ 390 ኪሎ ግራም ክብደት አለው ተብሏል።
በጠጨማሪም ግዙፉ ወፍ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ዋይ-20ኤ" የተሰኘው ግዙፉ የቻይና ወታደራዊ አውሮኘላንም በቻይና ኤር ሾው ላይ ለእይታ ቀርቧል።