ቻይና ሜሲና ክለቡ ኢንተርሚያሚ “ልዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት አላቸው” ስትል ወቀሰች
አርጀንቲናዊው ተጫዋች በሆንግ ኮንግ ጉዳት እንዳጋጠመው ገልጾ ሳይሰለፍ በጃፓኑ የወዳጅነት ጨዋታ መሰለፉ ነው ቤጂንግን ያስቆጣው
ሜሲ የቻይና ደጋፊዎቹን ይቅርታ ቢጠይቅም ከጃፓኑ ጨዋታ በኋላ ጉዳዩ ዳግም መነጋገሪያ ሆኗል
አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በጃፓን በተካሄደ የወዳጅነት ጨዋታ መሰለፉ ቻይናውያን ደጋፊዎቹ የሴራ ትንታኔ ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷል።
ሜሲ በሆንግ ኮንግ ከ38 ሺህ አድናቂዎቹ በተገኙበት የወዳጅነት ጨዋታ አለመሰለፉና በጉጉት የሚጠብቁትን ደጋፊዎች በስታዲየም በመዘዋወር ስላምታ አለመስጠቱ ደጋፊዎችን ማበሳጨቱ ይታወሳል።
በወቅቱ ጉዳት እንደገጠመው በመግለጽ ደጋፊዎቹን ይቅርታ ጠይቆ በሌላ ጊዜ ወደ ሆንግ ኮንግ እንደሚመለስ ባሳወቀ በሶስት ቀናት ልዩነት በጃፓን በተደረገ ጨዋታ መሰለፉ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አነጋጋሪ አድርጎታል።
የቻይና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የሆነው ግሎባል ታይምስ ባወጣው ሰፋ ያለ ጽሁፍም ሜሲ ባለፉት ስድስት የኢንተርሚያሚ የቅድመ ውድድር የወዳጅነት ጨዋታዎች ያልተሰለፈው በሆንግ ኮንግ ብቻ ነው ብሏል።
ከእግርኳስ ብቃቱ ባሻገር ስብዕናው ለበርካቶች አርአያ እንደመሆኑ በሆንግ ኮንግ ይህን የሚመጥን ተግባር ማሳየት ይገባው ነበር ያለው ግሎባል ታይምስ፥ ከአድናቂዎቹ ጋር ለመገናኘት አለመፍቀዱ ቻይናውያንን ማስቆጣቱን አውስቷል።
ከ12 ስአት በላይ ተጉዘው ተጫዋቹን ለመመልከት ስታዲየም የተገኙ አድናቂዎቹን ሰላምታ ለመስጠት እንኳን አለመፍቀዱ ለተተኪ ስፖርተኞች አርአያ የማይሆን ድርጊት መሆኑንም ነው ያብራራው።
በቶኪዮ በተካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ ለ30 ደቂቃዎች ተሰልፎ ሲጫወት በጥሩ ጤንነት ላይ መሆኑ ያስታውቅ እንደነበር በመጥቀስም በሆንግ ኮንግ ያልተሰለፈበት ምክንያት “ልዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት ይኖረው ይሆን?” የሚለውን የበርካቶች ጥርጣሬ ያጎላ ነው ብሏል።
ሜሲና ክለቡ ኢተርሚያሚ ሆንግ ኮንግን ሆን ብለው “ለማዋረድ” ነው ይህን ያደረጉት የሚል ድምዳሜ ላይም ደርሷል።
ባለፈው አመት አርጀንቲና ከአውስትራሊያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ስታደርግ ከ68 ሺህ በላይ ቻይናውያን ሜሲን ለመመልከት እስከ 680 ዶላር ከፍለው ስታዲየም ገብተው እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።
የሁዋዌ፣ ቼሪ፣ ቴንሴንት እና ሌሎች ግዙፍ የቻይና ታዋቂ ምርቶችና አገልግሎቶች አስተዋዋቂው ሜሲ በመጋቢት ወር ወደ ቻይና ሲመለስ ያስከፋቸውን ደጋፊዎች ለመካስ እንደሚሰራ ተናግሯል።
ተጫዋቹ ዌቦ በተሰኘው የቻይና ማህበራዊ ትስስር ገጽ በሆንግ ኮንግ ያልተሰለፈበትን ምክንያት ባሰፈረበት ጽሁፍ ስር ከ140 ሺህ በላይ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
አንዳንዶቹ ድጋፋቸውን ቢገልጹለትም አብዛኞቹ ግን በተለይ በጃፓኑ ጨዋታ ከተሰለፈ በኋላ በስድብ እየወረፉት ነው ተብሏል።