ቻይና የቡድን ሰባት ሀገራት ዲሞክራሲን ለማስተማር ብቁ አይደሉም አለች
ዲሞክራሲ ለምዕራባዊያን በሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ጣልቃ መግቢያ መሳሪያቸው ነው ተብሏል
በሆንግ ኮንግ በተደረገ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ ማዕከላዊ መንግስትን የሚደግፉ ዕጩዎች አሸንፋዋል
ቻይና የቡድን ሰባት አገራት ዲሞክራሲን ለማስተማር ብቁ አይደሉም አለች፡፡
በሆንግ ኮንግ በተደረገ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ የማዕከላዊ ቻይና መንግሥት ደጋፊ የሆኑ ዕጩዎች አሸንፈዋል።
ይሄንንም ተከትሎ ምዕራባዊያን ሀገራት የሆንግ ኮንግ ምርጫን ዲሞክራሲያዊ አይደለም በሚል ትችቶችን በመሰንዘር ላይ ሲሆኑ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዛኦ ሊጂያን እንዳሉት አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ዲሞክራሲን ለማስተማር ብቁ አይደሉም ብለዋል፡፡
ዲሞክራሲ ለምዕራባዊያን ሀገራት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ በሌላ ሉዓላዊ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መንገዳቸው መሆኑንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው እሁድ በቻይና አንድ አካል በሆነችው ሆንግ ኮንግ ግዛት የተካሄደውን የህግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ በማጣጣል ላይ ናቸው የሚሉት ቃል አቀባዩ ምዕራባዊያን ይሄንን የሚያደርጉት ምርጫው እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ባለመሄዱ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ስለ ዲሞክራሲ ከማውራታቸው በፊት በመጀመሪያ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት መከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን እና በአገራቸው ያሉተን የፖለቲካ ውጥረቶችን ጨምሮ በዜጎቻቸው መካከል ያለውን መድሎ ለማስቆም ይስሩ ሲሉ ወርፈዋል፡፡
በሆንግ ኮንግ በተካሁደው የታችኛው የህግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ የቻይና ማዕከላዊ መንግስትን አቋም የሚደግፉ እጩዎች 90 በመቶውን መቀመጫ ያሸነፉ ሲሆን የምርጫው ውጤት ምዕራባዊያንን አላስደሰተም፡፡
የምዕራባዊያን አገራት ባሳለፍነው እሁድ በተካሄደው ምርጫ ላይ የቻይና ማዕከላዊ መንግስት ተጽዕኖ አድርጓል፣የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው እና ሌሎች ትችቶችን በቤጂንግ ላይ ሰንዝረዋል፡፡
ሆንግ ኮንግ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረች ሲሆን ከፈረንጆቹ 1997 ዓመት ጀምሮ ቻይና ተረክባ በማስተዳደር ላይ ስትሆን አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን አገራት ሆንግ ኮንግ የቻይና አካል አይደለችም በሚል ቀጥታ ግንኙነት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ይህ ድርጊት ቻይናን ያስቆጣ ሲሆን በየጊዜው አሜሪካ እና ምዕራባዊያን ሀገራት ከቻይና የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን እንዲሰበስቡ በማጠንቀቅ ላይ ትገኛለች፡፡