ቻይና፤ የቡድን 7 አባል ሀገራት “ዓለምን መናቅ” አይችሉም አለች
በቻይና ጉዳይ የሚደረግ ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ያልተጠበቀ አደጋ እንደሚያስከትልም አስጠንቅቃለች
ቡድን 7 አለም አቀፍ ጉዳዮችን በብቸኝነት የሚቆጠጠርበትና ሌሎች ሀገራትን የሚያንገላታበት ጊዜ አልፏል ብላለች
የቡድን 7 አባል ሀገራት በሌሎች ሀገራተ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የመግባት መብት እንደሌላቸው ቻይና አስታወቀች።
ቻይና ይህንን ያለችው የቡድን ሰባት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባደረጉት ስብሰባ “ቤጂንግ አስገዳጅ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች” ትተገብራለች ሲሉ መተቸታቸውን ተከትሎ ነው።
- ቻይና ከደቡብ ቻይና ባህር ጋር በተያያዘ የአውሮፓ ህብረትን አስጠነቀቀች
- በተመድ ስብሰባ ሩሲያ፣ ቻይና እና ህንድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን ተቃወሙ
የቡድን ሰባት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ስብሰባ ባስተናገደችው ብሪታኒያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ባወጣው መግለጫው፤ “ቡድን 7 አለም አቀፍ ጉዳዮችን በብቸኝነት የሚቆጠጠርበት እና ሌሎች ሀገራትን እንደፈለገ የሚያንገላታበት ጊዜ አልፏል” ብሏል።
የሚመለከታቸው ሀገራት አለም አቀፍ ህግን እንዲያከብሩ ያሳሰበው መግለጫው፤ ቻይናን ማጣጣል፣ በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባት እንዲሁም በቻይና እና በሌሎች አገሮች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ችግር መፍጠርን እንዲያቆሙ አሳስቧል።
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩዝ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ስብሰባ ዙሪያ በትናትናው እለት መግለጫ አውጥተዋል።
በመግለጫውም “የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቻይና አስገዳጅ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ ስጋታችንን ገልፀዋል” ያሉ ሲሆን፤ በደቡብ ቻይና ባህር እና በታይዋን ባለው ውጥረት ዙሪያ መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
ቻይና በበኩሏ እነዚህ ጥያቄዎች አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ እና ካናዳን በአባልነት ያቀፈው የቡድን ሰባት ጉዳይ አይደሉም የሚል አቋም ይዛለች።
“በምስራቅ እና እና ደቡብ ቻይና ባህር ሁኔታ ላይ በውጭ ሀይሎች የሚደረግ ማንኛውም ጣልቃ ገብነት በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ላይ ያልተጠበቀ አደጋን ሊያስከትል ይችላል” በማለትም ቻይና አስጠንቅቃለች።
የቻይና መንግስት በሀገሩ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በራሱ መንገድ ምክክር እና ድርድሮችን ተጠቅሞ እንደሚፈታም በብሪታኒያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ አስታውቋል።