አብዛኞቹ የቡድን-20 ሀገራት ለዩክሬን ጦርነት ሩሲያን ሲያወግዙ ቻይና የተለየ አቋም ይዛለች
ህንድ ሩሲያን ባወገዘው ስብሰባ ላይ ገለልተኛ ሃሳብ አንጸባርቃለች
ጀርመን፤ ቻይና የማጠቃለያ መግለጫውን ለመቀላቀል ፈቃደኛ አለመሆኗ “አሳዛኝ ነው” ብላለች
የቡድን -20 አባል ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች ስብሰባ በህንድ በቤንጋሉሩ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡
ስብሰባው በቁልፍ የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ቢታወቅም፤ የዩክሬን ጉዳይ ዋነኛ የአባል ሀገራቱ መወያያ አጀንዳ ሆኖ መምጣቱ የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
- ኢትዮጵያን ሩሲያ ከዩክሬን እንድትወጣ የሚጠይቀውን የተመድ የውሳኔ ኃሳብ በድምጸ ተአቅቦ አለፈች
- ጀርመን ሰራሹ ታንክ በዩክሬን ጦርነት እጅግ ተፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የስብሰባው አዘጋጅና የቡድን-20 ሊቀመንበር ህንድ በውይይቱ የዩክሬን ጉዳይ እንዳይነሳ ግፊት አድርጋ የነበረ ቢሆንም፤ ምዕራባውያኑ ውግዘትን ያላካተተ ማንኛውንም የስብሰባው ውጤት ሊደግፉ እንደማይችሉ አሳስበዋል።
በዚህም በልዩነት የታጀበ የማጠቃለያ ሪፖርት ያወጣችው ህንድ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ውይይት አብዛኛኞቹ የቡድን-20 ሀገራት ለዩክሬን ጦርነት ሩሲያን ማውገዛቸውንና ቻይና የተለየ አቋም በመያዝ ከሞስኮ ጎን መቆሟ አስታውቃለች፡፡
"አብዛኞቹ አባላት በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ ስቃይ እያስከተለ እና በአለም አቀፍ ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉትን ብልሽቶች እያባባሰ ያለውን የዩክሬን ጦርነት አጥብቀው አውግዘዋል" ብላለች ህንድ ባወጣችው መግለጫ፡፡
በውይይቱ የተወገዘቸውን ሩሲያ ለመቅጣት ያስችላሉ የተባሉ የተለያዩ ኃሳቦች ተንጸባርቀዋልም ነው የተባለው፡፡
ቻይና እና ሩሲያ የቡድን -20 አባል ሀገራት ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ ፊርማቸውን ለማኖር ፈቃደኛ እንዳልሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ሩሲያ እና ቻይና የ ቡድን-20 መድረክ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እንዲወያይ አይፈልጉም ።
የቡድን-20 አባል ሀገራት ባሳለፍነው ወርሃ ህዳር በኢንዶኔዥያ ባሊ ባካሄዱት ስብሰባ ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
አለም አቀፍ የኢኮኖሚ ቀውሶችን ለመቅረፍ በሚል ከተቋቋመ ሁለት አስርት አመታት ያስቆጠረው ቡድን-20 ለዩነቶች ቢንጸባረቁበትም በቁልፍ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እየመከረ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ አሁንም እየታገለ መሆኑ ይነገራል፡፡
የህንድ ፋይናንስ ሚኒስትር ኒርማላ ሲታራማን የአሁኑ የስብሰባ ውጤትን በተመለከተ ሲናገሩ “አሁን ያወጣነው የስብሰባው ውጤት መግለጫ እንጅ የጋራ መግለጫ የምንለው አይደለም፤ ያም ሆኖ ሁሉንም ሚኒስትሮች በቦርድ ላይ በማሳረፍ የተወሰነ መሻሻል ያደረግን ይመስለናል”ብለዋል፡፡
የጀርመኑ የገንዘብ ሚኒስትር ክርስቲያን ሊንደርነር ቻይና የማጠቃለያ መግለጫውን ለመቀላቀል ፈቃደኛ አለመሆኗ “አሳዛኝ ነው” ሲለ ተደምጠዋል።
የጃፓኑ የፋይናንስ ሚኒስትር ሹኒቺ ሱዙኪ በበኩላቸው "ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት ለቡድመን-20 ገንቢ ውይይት ለማድረግ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፤ ድርጊቱ የአለምን ስርዓት የሚያናጋ መሆኑን በመጠቆም፡፡
ማንኛውም መግለጫ ሩሲያን ለማውገዝ “በጣም አስፈላጊ ነው” ያሉት ደግሞ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ጃኔት የለን ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለዩክሬን ጦርነት ሩሲያን ተጠያቂ ማድረጉ ተገቢ አይደለም የምትለው ህንድ ለጉዳዩ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄን መሻት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን በመግለጽ ገለልተኛ አቋም አራምዳለች፡፡
ሞስኮ ጦርነቱን በማቆም ወታደሮቿን ከዩክሬን እንድታስወጣ የተባበሩት መንግስታት ሃሙስ እለት በአብላጫ ድምጽ ባጸደቀው ውሳኔ ሃሳብ ላይ ቻይና እና ህንድ በድምጸ ተአቅቦ ማለፋቸው አይዘነጋም፡፡
ከቡድን-7 ሀገራት በተጨማሪ የቡድን-20 አባል ሀገራት የሆኑ አውስትራሊያ፣ ብራዚል እና ሳዑዲ አረቢያ የውሳኔ ሃሳቡን በድምጸ ተአቅቦ ካለፉት ሀገራት መካካል ይጠቀሳሉ፡፡
የቡድን-20 አባል የሆነችው ግን የ ቡድን-7 አባል ያልሆነችው ሩሲያ ምዕራበውያውን “ወረራ ነው” እያሉ የሚጠሩትን የዩክሬን ጦርነት “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ስትል እንደምትጠራው ይታወቃል፡