የአሜሪካና ጀርመን መሪዎች ወደ “ኒውክሌር ጦርነት” እንዳንገባ ኃላፊነታቸውን ይወጡ - ሜድቬዴቭ
ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፤ በቅርቡ ሩሲያ ከተሸነፈች የኒውክሌር ጦርነት አይቀሬ ነው ማለታቸው ይታወሳል
የአሜሪካና ጀርመን መሪዎች "የኒውክሌር ሰዓቱን እንዲያቆሙ" ሲሉም ጠይቀዋል ሜድቬዴቭ
ዩክሬንን ሽፋን ያደረገው የሩሲያና ምዕራባውያን ፍጥጫ ወደ ኒውክሌር ጦርነት ሊወስድ ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
በዚህ ስጋት የገባቸው የሩሲያ የጸጥታ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፥ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ወደ ኒውክሌር ጦርነት እየወሰደ ያለውን ሁኔታ እንዲያቆሙት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀገራቱ መሪዎች "የኒውክሌር ሰዓቱን እንዲያቆሙ"ም ጠይቀዋል የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የፑቲን የቅርብ ሰው እንደሆኑ የሚነግርላቸው ሜድቬዴቭ፡፡
ሜድቬዴቭ ይህ ያሉት የሩሲያው ዓለም አቀፍ የዜና ወኪል “ስፑትኒክ” ፤ “በሞስኮ እና በምዕራናውያን ያለው ውጥረት እንዴት ማርገብ ይቻላል ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው በሰጡት ምላሽ ነው፡፡
አሁን ለተፈጠረው ውጥረት ባለቤቶቹ ባይደን እና ሾልዝ ናቸው ያሉት ሜድቬዴቭ፤ በዩክሬን ጉዳይ መክሰራቸውን አውቀው ዓለምን ወደ ቀውስ የሚወስደውን “የምጽአት ቀን ማስቀረት ይችላሉ”ም ብለዋል፡፡
ስፑትኒክ የአቶሚክ ሳይንቲስቶች ቡድን መረጃን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ዓለም ወደ ቀውስና ውድመት ልትገባ አደገኛ ሁኔታ ላይ ተደርሷል፡፡
የምጽአት ቀን ሊመጣ “ የኒውክሌር እኩለ ሌሊት” ላይ ነንም ብሏል የሳይንቲስቶቹ ቡድን፡፡
በዩክሬን ምድር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሞስኮ ያሰበቸውን በቀላሉ ለማሳካት እንደማትችል የገባቸው ሜድቬዴቭ፤ ሀገራቸው በጦርነቱ ከተሸነፈች የኒክሌር ጦር መሳሪያዋን እንደምትጠቀም ያስጠነቀቁት ባሳለፍነው ሐሙስ እንደነበር አይዘነጋም፡፡በዩክሬን ያለው ጦርነት እንዲባባስ በማድረግ ዋነኛ ተጠያቂዎቹ ምዕራባውያን መሆናቸውም ጭምር በመግለጽ፡፡
“በምዕባውያን ኃይል የሩሲያ ግስጋሴ የሚቀለበስበት ሁኔታ ከተፈጠረ የኒውክሌር ጦርነት ይጀመራል” ሲሉም ነበር የተናገሩት የሩሲያ የጸጥታ ምክር ቤት ምክትል ኃላፊው፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት/ ኔቶ/ ለዩክሬን ጦር የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተም "ኒውክሌር የታጠቁ ኃይሎች እጣ ፈንታቸውን በሚወስኑ ትላልቅ ጦርነቶች አይሸነፉም" ብለዋል።
ሜድቬዴቭ የሩሲያ የጸጥታ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው ከመሾማቸው በፊት እንደፈረንጆቹ ከ2008 እስከ 2012 በፕሬዝዳንትነት እንዲሁም እስከ 2020 በጠቅላይ ሚኒስትርነት የኃላፊነት ቦታዎች ሀገራቸውን ያገለገሉ አንጋፋ ፖለቲከኛ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
የክሬምሊን ባለስልጣናት በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ አስበው በዩክሬን ላይ የጀመሩት ወታደራዊ ዘመቻ እንዳሰቡት ሳይሆን ሀገሪቱን በከፍተኛ የምዕራባውያን ጫና እንድትወድቅ ያደረገና መፍትሄ ያልተበጀለት ደም አፋሳሽ ጦርነት ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡