ኢትዮጵያን ሩሲያ ከዩክሬን እንድትወጣ የሚጠይቀውን የተመድ የውሳኔ ኃሳብ በድምጸ ተአቅቦ አለፈች
የ200ሺህ ሰዎች ህይወት የቀጠፈው የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ድፍን አንድ አመት ሆኖታል
ኤርትራ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሩሲያን በመደገፍ ድምጽ ሰጠች
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፤ ከተጀመረ አንድ ዓመት የሆነውን የዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ ሃሙስ እለት የቀረበውን የውሳኔ ኃሳብ በከፍተኛ ድምጽ አጽድቋል።
በዚህም ሩሲያ ጦርነት አቁማ ወታደሮቿን ከዩክሬን እንድታስወጣ እና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ለሚጠይቀው የውሳኔ ሃሳብ 141 ሀገራት የድጋፍ ድምጽ ሲሰጡ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 32 ሀገራት በድምጽ ተአቅቦ አልፈውታል።
ኤርትራ፣ ማሊ፣ ቤላሩስ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያ፣ እና ኒካራጓ ደግሞ የተመድ የውሳኔ ኃሳብ በመቃወም ድምጽ የሰጡ ሲሆን፤ ለሩሲያ አጋርነታቸውንም አሳይተዋል።
- ኢትዮጵያ ተመድ ሩስያ ለዩክሬን ካሳ እንድትከፍል ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በመቃወም ድምጽ ሰጠች
- ኢትዮጵያ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሩሲያን በመደገፍ ድምጽ ሰጠች
ኢትዮጵያን ጨምሮ የውሳኔ ሃሳቡን በድምጸ ተአቅቦ ካለፉት 32 ሀገራት ግማሽ የሚሆኑት ከአፍሪካ ናቸው ተብሏል።
ሀገራቱ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኣፍሪካ፣ አልጀርያ፣ አንጎላ፣ ብሩንዲ፣ ናሚቢያ፣ ማእከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮንጎ-ብራዛቪል፣ ጋቦን፣ ጊኒ፣ ሞዛምቢክ፣ ሱዳን፣ ቶጎ፣ ኡጋንዳ እና ዚምባብዌ መሆናቸውም ነው የተገለጸው።
ናይጀርያ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ግብጽ፣ ጋና እና ኬንያ የውሳኔ ኃሳቡን ከደገፉት የአፍሪካ ሀገራት ናቸው።
ይህ ቁጥር በጥቅምት ወር ከነበረውና ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶች መያዟን ለማውገዝ ከተላለፈው የውሳኔ ሃሳብ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ሩሲያ የዩክሬን ግዛቶችን መቆጣጠሯን ባወገዘው ጉባኤ ላይ ቤላሩስ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ሶሪያ እና ኒካራጓ ውሳኔውን ሲቃወሙ ማሊ እና ኤርትራ በድምጸ ተአቅቦ ካለፉት ሀገራት መካከል ነበሩ።
ባለፈው መጋቢት ወር ሩሲያ ከዩክሬን እንድትወጣ ተመድ ባሳለፈው የውሳኔ ሃሳብም እንዲሁ ኒካራጓ እና ማሊ በድምጸ ተአቅቦ ሲያልፉት ኤርትራ መቃወሟ አይዘነጋም።
ውሳኔዎቹ በአለም አቀፍ ህግ ውስጥ አስገዳጅ ባይሆኑም፤ የሩስያ እርምጃ ዓለም አቀፋዊ ተግሳጽ እንዳጋጠመውና ፖለቲካዊ ትርጉሙ ከፍተኛ እንደሆነ አመላካች ናቸው።
አስገዳጅ እርምጃዎችን መውሰድ የሚችለው ሩሲያ ቋሚ አባል የሆነችበትና ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን በተጎናተፈችበት የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ነው።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ውሳኔው “ትልቅ የዓለም አቀፍ ድጋፍ ምልክት ነው” ብለውታል።
ከተጀመረ ድፍን አንድ አመት የሆነውና በሁለቱም ወገን 200 ሺህ ሰዎች እንደሞቱበት የሚነገርለት የዩክሬን ጦርነት አሁንም የዓለም ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።