የታይዋን ጉብኝታቸው የቀጣናውን ነባር ሁናቴ ለመቀየር በማሰብ የተደረገ እንዳልሆነም ተናግረዋል
በደቡብ እስያ ቀጣና (ኢንዶ-ፓስፊክ) ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ቻይና ታይዋንን ከዓለም አቀፍ መድረኮች አስገልላ ልታስቀራት አትችልም ሲሉ ተናገሩ።
ፔሎሲ ይህ እንዲሆን "አሜሪካ አትፈቅድም" ብለዋል።
ቻይና በቅርቡ እንኳን፤ ታይዋን በዓለም ጤና ድርጅት መድረኮች እንዳትሳተፍና ስሟ እንኳን እንዳይነሳ ማድረጓን የተናገሩት አፈ ጉባኤዋ ይህ በሌሎች አጋጣሚዎችም የሆነ ነው ብለዋል።
ታይዋን በእንዲህ ዐይነት መድረኮች እንዳትሳተፍና ባለስልጣናቶቿ እንዳይጓዙ ሊያደርጉ ቢችሉም እንኳን እኛን ግን ሊያስቀሩን አይችሉም ሲሉም ነው ፔሎሲ የተናገሩት።
"የጉዞ እቅዳችንን አያወጡልንም" ሲሉም ተናግረዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት ወደ ታይዋን መጓዛቸው እንደሚቀጥልና የታይዋን ባለስልጣናትም ይሄንኑ እንደሚያደርጉም ነው የገለጹት ፔሎሲ።
ጉብኝታቸው ቀደም ሲል ከታይዋንም ሆነ ከቻይና ጋር በተደረጉ ስምምነቶች መሠረት የተከናወነ እንጂ የታይዋንንም ሆነ የቀጣናውን ሁናቴ ለመቀየር በማሰብ የተካሄደ እንዳይደለም ገልጸዋል።
ሆኖም "እንዳያችሁት ቻይና ጉብኝቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወታደራዊ ልምምዶችን ጨምሮ ሌሎች ሙከራዎችን አደረገች" ሲሉ ተናግረዋል አፈ ጉባኤዋ።
ቻይና የፔሎሲ ጉብኝት በሉዓላዊነቴና ግዛታዊ አንድነቴ ላይ የተቃጣ ነው በሚል በጽኑ ከማውገዝ አልፋ ወታደራዊ ልምምዶችን ማድረጓ እና ሚሳኤል ጭምር መተኮሷ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም በቀጣናው ከፍተኛ ውጥረት የነገሰ ሲሆን በርካታ በረራዎችም ተሰርዘዋል።